በገጠር መንገዶች ላይ ድልድይ ባለመገንባቱ ተቸግረናል – የጋሰራ ወረዳ አርሶ አደሮች

56

ጎባ ጥር 13 ቀን 2012 በየአካባቢያቸው የተገነቡ የገጠር መንገዶች ድልድይ ስላልተሰሩላቸው ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መጋለጣቸውን በባሌ ዞን የጋሰራ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

የዞኑ መንገዶች ባለስልጣን የተሟላ አገልግሎት የማይሰጡ መንገዶችን ችግር  ለመፍታት እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡

ከነዋሪዎቹ አንዳንዶቹ እንዳስረዱት ያለ ድልድይ የተገነቡት መንገዶች ሥራ ባለመጀመራቸው ችግራቸውን እንዳልተፈታ ገልጸዋል።

የሚመለከታቸው አካላት ለችግሩ መፍትሄ እንዲፈልጉም ጠይቀዋል።

በወረዳው የዋሪዮ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ከድር ሁሴን እንደገለጹት ጋሰራን ከሲናና ወረዳ ጋር የሚያገናኝ የገጠር መንገድ ቢሰራም፤ በዌብ ወንዝ ላይ ድልድይ ባለመገንባቱ መንገዱ አገልግሎት አይሰጥም፡፡

በዚህም የአካባቢው ምርቶችን በወቅቱ ለገበያ ለማቅረብም ሆነ ምጥ የያዛቸውን እናቶችን ጭምር ወደ ህክምና ተቋም ለማድረስ መቸገራቸውን ገልጸዋል።

 ከዋሪዮ ቀበሌ እስከ ዞኑ ዋና ከተማ ሮቤ ድረስ 15 ኪሎ ሜትር ብቻ የሚፈጀውን መንገድ ድልድይ ስላልተሰራለት በሌላ አቅጣጫ እስከ 60 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ለመጓዝ ተገደናል ያሉት ደግሞ ሌላው የወረዳው ነዋሪ አቶ መሐመድ አህመድ ናቸው፡፡

ድልድዮች ተጠናቀው ለአገልግሎት ባለመብቃታቸው ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ ከመቸገራቸውም በላይ፤ በእንጨት ላይ ወንዙን ለመሻገር በሚደረገው ሙከራ ለሚጠፋው ሕይወት ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡

የሽፋሮ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ፋጡማ አማን በበኩላቸው ወረዳው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና ሌሎች የእንስሳትና የተፈጥሮ ሀብት ጸጋ ቢኖረውም፤ ድልድይ ባለመኖሩ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ችግሩን በማስመልከት የአካባቢው ነዋሪዎች ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ቢያቀርቡም፤ እስካሁን ተገቢ ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዌብ ወንዝ ላይ ድልድይ ቢገነባ ኖሮ፤ ከሮቤ ጋር በቅርብ ርቀት ለመገናኘት እንችል ነበር ያሉት ደግሞ ሌላው የወረዳው ነዋሪ አቶ ኡስማን አደም ናቸው፡፡

መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በገባው ቃል መሠረት ለችግሩ እልባት እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡

የጋሰራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኡስማን ኡመር  በሰጡት ምላሽ የአካባቢው ማህበረሰብ ከድልድዮችና ሌሎች የገጠር መንገዶች ጋር በተያያዘ የሚያነሳቸው ቅሬታዎች አግባብነት እንዳላቸው ያምናሉ፡፡

ባለፉት ዓመታት የአርሶ አደሩን የመንገድ ልማት ጥያቄ ተደራሽ ለማድረግ በሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም 200 ኪሎ ሜትር መንገድ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳን ወረዳው ገጠርን ከከተማ ጋር ለማስተሳሰር መልካም ሥራዎች ቢከናወኑም፣ በዌብ ወንዝ ላይ ትላልቅ ድልድዮች ባለመሰራታቸው ማህበረሰቡ በክረምት ወቅት የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት እንደሚቸገር አስረድተዋል፡፡

በተለይ የአካባቢው ማህበረሰብ በዌብ ወንዝና በሌሎች ትላልቅ ወንዞች ላይ የሚሰሩ ድልድዮች ስፋታቸው ከ20 ሜትር በላይ በመሆናቸው በወረዳው አቅምና በጀት መስራት እንደማይቻል አስረድተዋል።

ለዞኑ መንገዶች ባለሥልጣን ችግሩን አሳውቀን በጋራ  እልባት ለመፈለግና ተቀናጅተው መሥራት  እንደሚሹ እንዳረጋገጡላቸው አቶ ኡስማን ተናግረዋል፡፡

የዞኑ መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊ አቶ ታጁዲን ሀሱ የጋሰራ ወረዳን ጨምሮ የዞኑ ማህበረሰብ በገጠር መንገድ ተደራሽነት መርሃ ግብር ላይ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን ክፍተቶች በጥናት ለይቶ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ከዚህ በፊት የግንባታ ስራቸው ተጠናቀው ድልድይ ባለመሰራቱ ለአገልግሎት ክፍት ያልተደረጉ መንገዶችን ቅድሚያ በመስጠት ክረምት ከበጋ አገልግሎት የሚያገለግሉ የ20 ድልድዮች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ኅብረተሰቡ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያነሳበት ጋሰራን ሲናና ወረዳዎችን በቅርብ ርቀት የሚያገናኘውንገ በዌብ ወንዝ ላይ ድልድይ በቀጣይ ዓመት ለመስራት ዲዛይን እየተዘጋጀ  መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በባሌ ዞን ከ2004 ወዲህ በሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ተደራሽነት መርሃ ግብር 2ሺህ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ መንገድ ተገንብቶ ለአርሶና አርብቶ አደሩ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ከዞኑ መንገዶች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም