የብዝሃ ህይወትን መንከባከብና መጠበቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ዘላቂ ጥቅም አለው-የባዮ ዳይቨርሲቲ ኢንስቲትዩት

98
አዲስ አበባ ሰኔ18/2010 የብዝሃ ህይወትን መንከባከብና መጠበቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ዘላቂ ጥቅም ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተገለጸ። 25ኛውን የ“ባዮ ዳይቨርሲቲ” (ብዝሃ ህይወት) ቀንን በማስመልከት በአካባቢ፤ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር በዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶች ዙሪያና በብዝሃ ህይወት አጠባበቅ ላይ ለሶስት ቀን የሚቆይ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማርየው በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የብዝሃ ህይወት ስምምነት ከፈረመች በኋላ የታዩ በርካታ ለውጦች አሉ። በዚህም ወደ 89 አዝርዕትና የሆርቲ ካልቸር ዝርያዎች የተሰበሰቡ ሲሆን፤ ከ80 ሺህ በላይ የሚሆኑ ናሙናዎችም እንዳሉ ገልጸዋል። የ አሶሴሽን ፎር ዴቬሎፕሜንት ኤንድ ባዮ ዳይቨርሲቲ ኮንዘርቬሽን ዳይሬክተር አቶ ከተማ ፉፋ በበኩላቸው፤ "አገር በቀሉ ድርጅታችን ከኢትዮጵያ የብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ለብዝሃ ህይወት ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ ላይ ይገኛል" ይላሉ። በተለይ በየጊዜው እየተራቆተ ያለውን የብርቅዬ እንሰሳት መኖሪያ የሆነውን ደን መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል። በመሆኑም ፓርኮች አካባቢ የልማት ስራን  በመስራትና የግንዛቤ ማስጨበጫን በመፍጠር ሰፊውን የብዝሃ ህይወት  ሃብትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ኢንስቲትዩቱ እ.አ.አ 1994 ጀምሮ ለተቋቋመበት ዓላማ እየሰራ ሲሆን፤ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አዝርዕቶችን የማብዛት ስራ በተግባር ላይ አውሏል። በሌሎች ክልሎችም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብና ከብዝሃ ህይወት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ከተለያዩ አዝርዕትና ከሆርቲ ካልቸር ሌላ የደን፣የእጽዋት፤የእንስሳትና የደቂቅ አካላት ብዝሃ ህይወትም ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተጠቁሟል። ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥና የቆመለትን ዓላማ ለመፈጸም በብዝሃ ህይወት ላይ ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራ እንደሚገባም ተገልጿል። ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የአየር ለውጥን ተጽእኖ መቋቋም፤ የአካባቢ ሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ቴክኖሎጂን በየጊዜው ከእውቀት ጋር በማስፋት ረገድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መስራት እንዳለበትም ተገልጿል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም