ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእምነት የታነጸና በመልካም ስነ-ምግባር የተገነባ ሆኖ አገሩን መጠበቅ አለበት

78
አዲስ አበባ ጥር 12/2012 (ኢዜአ)  ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእምት የታነጸና በመልካም ስነ-ምግባር የተገነባ ሆኖ አገሩን መጠበቅ እንዳለበት አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተራ በዓል ታዳሚዎች ገለጹ። የጥምቀት ከተራ በዓል በየአካባቢው በሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች በተለያዩ መንፈሳዊ ስነ-ስርአቶችና ያሬዳዊ ዜማዎች ታጅቦና ደምቆ  በመላው ኢትዮጵያ እየተከበረ ይገኛል። በኢትዮጵያ የሚከበሩ ሐይማኖታዊ በዓላት ከእምነት ፋይዳቸው ባሻገር ባላቸው ባህላዊ ገጽታ በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኚዎች የሚታደሙባቸው ናቸው። ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ኢትዮጵያ አንድ ሆና የምትታይበት በመሆናቸው ህዝቡ በእምነት የታነጸ፣ በመልካም ስነ-ምግባር የተገነባና በማንነቱ የማይደራደር ሆኖ ሊጠብቃቸው እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይናገራሉ። በተለይም በአገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጠሩ ችግሮችና አለመግባባቶች ህዝቡ አንድነቱ ተሸርሽሮ እየመጣ መሆኑ ይስተዋላል። እነዚህ ነገሮች ለአገርም ሆነ ለህዝብ የማይጠቅሙ በመሆናቸው መከፋፈልና መለያየትን ብሎም ጥላቻን ማስወገድ እንዳለባቸውም ይናገራሉ። የዘንድሮው የጥምቀት በዓል የህዝቦች ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት የሚንጸባረቅበት ሆኖ መከበር እንዳለበት ገልጸዋል። አገር ሰላም ካልሆነ ሃይማኖትን ማስቀጠል የማይቻል በመሆኑ የአገርን ሰላም ለማስጠበቅ መትጋት እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል። ''ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ከትውልደ ወደ ትውልድ በማሻገር አገር የሚጠቅምና የሚጠብቅ  ትውልድ ማፍራት አለበት'' ብለዋል። በዓለ ጥምቀት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል በድምቀት የሚከበር በዓል ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም