ኢዴፓ በመስቀል አደባባይ የተፈጸመውን የቦምብ ጥቃት አወገዘ

76
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2010 የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በመስቀል አደባባይ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተጠራ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተፈፀመውን የቦምብ ጥቃት አወገዘ። የአዲስ አበባ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትም በደረሰው ጥቃት ህይወታቸውን ላጡና ለተጎዱ ወገኖች የተሰማውን ሃዘን ገልጿል። ኢዴፓ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ሰኔ 16 ቀን 2010  በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ  ላይ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ፣ ሰብዓዊነት የራቀውና ከኢትዮጵያዊያን ባህል የወጣ ተግባር መሆኑን አመልክቷል። ንፁሀን ዜጎችን የጥቃት ሰለባ በማድረግ የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ አይኖርም ያለው ኢዴፓ በተፈፀመው ጥቃት ህይወታቸውን ላጡና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል። መላው ህዝብ ከስሜታዊነት በፀዳና አገራዊ አንድነትን በሚያንፀባርቅ መንገድ የሚጠበቅበትን ሚና መጫወቱን ሊቀጥል እንደሚገባም ኢዴፓ አሳስቧል። በአገሪቱ የሀሳብ ልዩነት ያላቸው ቡድኖችና ግለሰቦች ልዩነቶቻቸውን በሰለጠነና ጊዜው በሚፈቅደው መንገድ በውይይት ለመፍታት እንዲጥሩም  አሳስቧል። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው መንግስት በድርጊቱ ፈፃሚዎች ላይ ለህዝብ ግልፅ በሆነ መልኩ ምርመራ በማድረግ ህግ ፊት እንዲያቀርባቸውም  ኢዴፓ ጠይቋል። የአዲስ አበባ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በበኩሉ በደረሰው ጥቃት የተሰማውን ሀዘን በመግለፅ ድርጊቱን በፅኑ አውግዟል። መንግስት በአገሪቱ ሰላምና አንድነትን ለማጎልበት የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቀው ምክር ቤቱ ይህ ጥረት ይሰምር ዘንድም የበኩሉን ሚና ለመጫወት ቃል ገብቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም