በሀረር በጥምቀት በዓል ላይ ጉዳት ለማድረስ የሞከሩ 20 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሀረር በጥምቀት በዓል ላይ ጉዳት ለማድረስ የሞከሩ 20 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
118
ሐረር ኢዜአ ጥር 12/2012 በሃረር የጥምቀት በዓል ላይ ሁከት በመፍጠር በሰዎች ላይ ጉዳት ለማድረስ የሞከሩ 20 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ረመዳን ኡመር ዛሬ እንደገለጹት ከጥር 10/2012 ጀምሮ አንዳንድ የጥፋት ተልዕኮ ያነገቡ አካላት በዓሉን ለማወክ ያደረጉት ጥረት በፀጥታ አካላትና በህብረተሰቡ ቅንጅት የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ለመቆጣጠር ተችሏል። እስከ አሁን ድረስም በድርጊቱ የተሳተፉ 20 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸው በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት በማጣራትና አስፈላጊው መረጃ በማሰባሰብ ተጠርጣሪዎቹ ለህግ እንደሚቀርቡ ተናግረዋል። በተፈጠረው የፀጥታ ችግርም 15 የጸጥታ አካላትን ጨምሮ በ19 ሰዎች ላይ ቀላል የአካል ጉዳት እንዳጋጠመና በንብረት ላይም ከፍተኛ የሆነ ጉዳት እንደደረሰ ኮሚሽነሩ ገልፀዋል። ለሕብረተሰቡ ትዕግስትና ትብብር ምስጋናቸውን የገለፁት ኮሚሽነር ረመዳን ይሄንኑ በማጠናከር ክልሉ የሚታወቅበትን የሰላም የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶችን እንዲያስቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በዛሬው እለትም ህብረተሰቡ እንደ ወትሮው ሁሉ ታቦታት ወደየደብራቸው በሰላም እንዲሽኙ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪያቸውን አቅርበዋል።