የልጆቻቸውን የአመጋገብ ሥርዓት በመሰተካከሉ በአካል ጥንካሬና በፍጥነት ለውጥ እንደታየባቸው ወላጆች ተናገሩ

75
መቀሌ ጥር 12/2012 (ኢዜአ)  የልጆቻቸውን የአመጋገብ ሥርዓት በማስተካከላቸው በአካል ጥንካሬና በፍጥነት ለውጥ እንደታያባቸው በትግራይ ክልል የሁለት ወረዳ እናቶች አስታወቁ። የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮጀክት የምክክር መድረክና የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል። በክልሉ የቆላ ተምቤንና ጠንቋ አበርገለ ወረዳዎች  በፕሮጀክቱ  የታቀፉ ሴት አርሶ አደሮች እንደመሰከሩት ፕሮጀክቱ የአመጋገብ ሥርዓትን አስመልክቶ የሰጣቸውን ትምህርት በመተግበራቸው ልጆቻቸው አካላዊ ጥንካሬና ቅልጥፍና አሳይተዋል። በቆላ ተምቤን ወረዳ የመንጂ ገጠር ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ብርሃን ተክለሃይማኖት በፕሮጀክቱ ከታቀፉ ሴት አርሶ አደሮች መካከል አንዷ ናቸው። የአምስት ወንድ ልጆች እናት መሆናቸውን የሚናገሩት  አርሶ አደሯ ፣የህጻናት መልካም አስተዳደግ ምስጢር ሆድ መሙላት ብቻ አለመሆኑን ከፕሮጀክቱ መማራቸውን ይናገራሉ። ህጻናትን ከግብርና ምርቶችና ከእንስሳት ተዋፀኦ እያቀያየሩና እያመጣጠኑ በመመገብ የአካል ብቃትና ለአዕምሮ ቅልጥፍና ትክክለኛ መንገድ መሆኑን በልጆቻቸው ማየታቸውን ገልጸዋል። ''በቤቴ ጓሮ ውስጥ ድንች፣ስኳር ድንችን ጨምሮ የተለያዩ የጓሮ አትክልትን አለማለሁ።ስራውን የጀመርኩት ከሦስት ዓመት በፊት ነው።ያለማሁትን የጓሮ አትክልት እየቀያየርኩና ከእንስሳት ተዋጽኦ ጋር በማደባለቅ ልጆቼን በየጊዜው መመገብ በመቻሌ እነሆ ዛሬ ልጆቼን መልካም የአካል ጥንካሬና የአእምሮ ቅልጥፍና እንዳላቸው ማረጋገጥ ችያለሁ'' ብለዋል። ያገኙትን መልካም ውጤት 25 ለሚሆኑ እማወራ አርሶ አደሮች በማካፈል በልጆቻቸው አመጋገብ ላይ ማስተካከያ እንዲያደርጉና የተመጣጠነ የአመጋገብ ሥርዓት እንዲከተሉ ማስተማራቸውንና ውጤት እንዳገኙትም ተናግረዋል። በጣንቋ አበርገለ ወረዳ ልዩ ስሙ አግበ በተባለው ገጠር ቀበሌ ነዋሪ የሚኖሩት እማወራ አርሶ አደር ወይዘሮ ጸዳል ተክለሃይማኖት በበኩላቸው ጥሩ ቁመናና አካላዊ ጥንካሬ ያለው ህጻን እንዲኖረን የተመጣጠነ የአመጋገብ ሥርዓት መከተል ወሳኝ ነው ይላሉ። ከፕሮጀክቱ ባገኙት ትምህርትና በተግባር ያገኙት ውጤት ይህንኑ ያመለክታል ብለዋል። ላለፉት ሦስት ዓመታት ያገኙትን ግንዛቤ በመተግበራቸውና በጓሮአቸው  የሚያለሙትን አትክልት ልጆቻቸውን ለአንድ ሺህ ቀናት በመመገባቸው ጤንነታቸው እንደተጠበቀ  አስታውቀዋል። ሌሎች 30 እማወራ አርሶ አደሮች ፈለጋቸውን ተከትለው በልጆቻቸው አመጋገብ ላይ ለውጥ እንዲያመጡ ማስተማራቸውን ወይዘሮ ጸዳል ተናግረዋል። ካለማቋረጥ የተመጣጠነ ምግብ ያገኙ ህጻናት ትምህርት የመቀበል አቅማቸውና ፈተናን የማለፍ ብቃታቸውን የላቀ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የጣንቋ አበርገለ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ገብረህይወት ዓለማየሁ ናቸው። በትምህርት ቤቱ ውስጥ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ከሚማሩ 1 ሺህ 200 ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተመጣጠነ ምግብ የሚያገኙበት የጓሮ አትክልት ልማት ፕሮጀክት ለመተግበር እየተሰራ መሆኑንም ርዕሰ መምህሩ አስረድተዋል። የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮጀክት ጽህፈትቤት ኃላፊ አቶ ፀጋዘአብ ሃይሉ በበኩላቸው የተከዜ ተፋሰስን ተከትለው የሚገኙ የትግራይ ክልል 13 ወረዳዎች ፕሮጀክቱ በሚያከናውነው የልማት ስራ መታቀፋቸውን ተናግረዋል። በወረዳዎች ውስጥ ከአንድ እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ክልል የሚገኙ ከ80 ሺህ በላይ ህጻናትን  እንደሚገኙ ያመለከቱት ኃላፊው፣ከህጻናቱ ውስጥ 62 በመቶ ያህሉ ለመቀንጨር አደጋ የተጋለጡ ናቸው ብለዋል። በክልሉ ያለው የመቀንጨር አደጋ 49 በመቶ መሆኑ ያስታወሱት አቶ ጸጋዘአብ፣በክልሉ በቀጣይ 15 ዓመታት ውስጥ የመቀንጨር ችግርን ወደ ዜሮ ለማውረድ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ መንግሥትና ከአፍሪካ ልማት ባንክ ለፕሮጀክቱ ስኬት 10 ቢሊዮን ብር በጀት ይጠበቃል ብለዋል። ለፕሮጀክቱ በየዓመቱ ከ133 ሚሊዮን ብር በላይ እየተመደበ ሥራ ላይ እየዋለ ነው ያሉት አቶ ፀጋዛኣብ፣ከበጀቱ ባለፈ ግን በየደረጃው የሚገኙ የግብርናና ገጠር ልማት፣የትምህርትና የውሃ ሃብት ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም