የጥምቀት በዓል ትህትናንና በጎነትን የምንማርበት ነው - ምዕመናን

54
ጥር 12/2012 (ኢዜአ)  በጥምቀት በዓል የሚታይ ትህትናና አብሮነት በእለት ተዕለት ህይወታችንም ሊዳብር ይገባል ሲሉ በጃን ሜዳ የጥምቀት በዓል ታዳሚያን ተናገሩ። ጥምቀት ለዕምነቱ ተከታዮች ልጅነት ያገኙበትና የዕዳ ደብዳቤያቸው የተደመሰሰበት መሆኑን የኃይማኖት አባቶች አስረድተዋል። በዓሉ እየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ መጠመቁን አስመልክቶ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የሚከበር በዓል ነው። እየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትን እራሱ ተጠምቆ በተግባር፣ በትምህርትና በትዕዛዝ እንደመሰረተውም የኃይማኖት አባቶቹ ያስረዳሉ። በተለይም ክርስቶስ እራሱ ተጠምቆ ሌሎች እንዲጠመቁ አርአያ የመሆኑን ያህል የእምነቱ ተከታዮችም በሁሉ ምግባራቸው ታዛዥነትን ሊማሩ እንደሚገባ ይመክራሉ። በተጨማሪም ክርስቶስ የፍቅር፣ የአብሮነትና የመተሳሰብ ምንጭ የሆነውን ትህትናን እንዳስተማረ እምቢተኝነትን በመተው ትህትናን እናጎልብት ብለዋል ታዳሚያኑ። በመሆኑም ምዕመናኑ የጥምቀትን በአል በአንድነት፣ በፍቅርና በትህትና የሚያከብርበትን በሌላም የእለት ተዕለት ተግባሩ ሊያጎለብተው እንደሚገባ ነው የገለጹት። ክርስቶስ አምላክነቱን ትቶ ዝቅ ብሎ በሰው እጅ ተጠምቆ ትህትናን እንዳስተማረን ዛሬም ወጣቶች በበዓሉ ወቅት ትህትናንና ዝቅ ብሎ ማገልገልን እተገበሩ መሆኑን ያነሳሉ። የተለያየ እምነት ተከታዮች የሚኖሩባት ኢትዮጵያ አንዱ የአንዱን እምነት በማክበር የነበረውን እሴት ማስቀጠል አለብን ብለዋል። ጥምቀት የአደባባይ በዓል እንደመሆኑም ከኃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሩ ማህበራዊ ፋይዳውም የጎላ መሆኑን የእምነቱ ተከታዮች ገልጸዋል። በዚህም ዘር፣ ሃይማኖት፣ ፆታና እድሜ ሳይለይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ታቦታት ወደ ከተራ ሲወርዱና ወደ ማደሪያቸው ሲመለሱ ለምዕመናኑ የውሃ፣ ምግብና ሌሎች አቅርቦቶችን ማድረጋቸው አንድነትን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም