ፊንላንድ በአራት መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገለጸች

192
አዲስ አበባ ጥር 12/2012 (ኢዜአ)  ፊንላንድ በአራት መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት አስታወቀች። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ ዘርፍ ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ማህሌት ሃይሉ የፊንላንድ የልማት ምክትል ሚኒስትር የሆኑትን ኤሊና ካልኩ ዛሬ  በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። የፊንላንድ የልማት ምክትል ሚኒስትር ኤሊና ካልኩ በኢትዮጵያ ስላለው ሁሉን አቀፍ ለውጥና ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ወሳኝ ሚና እየተጫወተች ላለችው ሚና አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ምክትል ሚኒስትሯ  በዚሁ ጊዜ ፊንላንድ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ ዩኒቨርሲቲ ለዩኒቨርሲቲ ትስስር እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ጾታዊ እኩልነት ከማስፈን ጋር በተያያዘ ተቀራርቦ ለመስራት ፍላጎት እንዳላትም ተናግረዋል። አምባሳደር ማህሌት በበኩላቸው ሁለቱ አገራት በሁሉም ዘርፍ መልካም የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዳላቸው አውስተዋል። አምባሳደሯ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ በመንግስት እየተወሰዱ ስላሉ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በተመለከተ  ገለጻ ማድረጋቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ኢትዮጵያ በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና የኢኮኖሚ ትስስር እንዲመሰረት እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተም ማብራሪያ እንደሰጡም በመግለጫው ተመልክቷል። በኢትዮጵያ እና በፊንላንድ መካከል ያለውን ግንኙነት በንግድ እና በኢንቨስትመንት ይበልጥ ለማጠናከር መስራት እንደሚያስፈልግም አምባሳደሯ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ እና ፊንላንድ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት ከጀመሩ እ.አ.አ ከ1959 ጀምሮ በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ በቅርርብ እና በትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኙ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል። በሌላ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ የዓለም አዕምሯዊ ንብረት ድርጅት ምክትል  ዳይሬክተር ሚስ ዋንግ ቢንይንግ የተመራ ልዑካን ቡድንን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። ወይዘሮ ሂሩት ኢትዮጵያ ከዓለም አእምሮዊ ንብረት ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሰራም በዚሁ ጊዜ  ገልጸዋል። የዓለም አዕምሮዊ ንብረት ድርጅት በማደግ ላይ ያሉ አገሮችን የቴክኖሎጅ እና አዕምሯዊ ንብረት ለማስጠበቅ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸው መሆኑንም ተናግረዋል። ሚስ ዋንግ ቢንይንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ሲጎበኙ ይህ የመጀመሪያቸው መሆኑን ገልጸው፤ በጉብኝታቸው ኢትዮጵያ ምድረ-ቀደምት ሀገርና በአሁኑ ወቅትም በአፍሪካ በፍጥነት እያደገች መሆኗ አስደሳች ነው ብለዋል። በድርጅቱ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ መናገራቸውንም ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም