የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን የግጭት ቀጠና የማድረግ ሙከራ ከሽፏል...አቶ አሻድሊ ሃሰን

129
አሶሳ፤ ጥር 12/2012 (ኢዜአ)  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝቦችን ከአጎራባች ክልሎች ህዝቦች በማጋጨት ሀገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ የተደረገው ጥረት ሳይሳካ መቅረቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ። በክልሉ አንድ ወረዳ እና 48 ቀበሌዎች በአዲስ መልክ ተዋቅረዋል። የክልሉ ምክር ቤት አምስተኛ አመት አስረኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ሲጀመር ርዕሰ መስተዳድሩ ያቀረቡት ያለፉት ስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ትኩረት ባጋጠሙ የፀጥታ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ነው። በክልሉ በ2012 ግማሽ በጀት አመት በመደመር እሳቤ ለተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ርብርብ ቢደረግም በዜጎች ግጭት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ያለሙ ሃይሎች ዘርን መሰረት ባደረገ ጥቃት የህዝቡን ህገ-መንግስታዊ ድሎች ለመደፍጠጥ መሞከራቸውን አስረድተዋል። "ሆኖም የክልሉ መንግስት በተለይም የክልሉ ህዝቦች ከአጎራባች ህዝቦች ጋር ያላቸውን የቆየ ግንኙነት ለማጠናከር የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በዕርቅና ይቅርታ ለመፍታት ያደረገው ጥረት ውጤት አስመዝግቧል"ብለዋል። የሀገር ሽማግሌዎች የሀይማኖት አባቶች የፀጥታ አስከባሪ አካላትን ጨምሮ የክልሉ ህዝብ በትዕግስት እና በሀገራዊ ሀላፊነት ላደረገው ተሳትፎም አመስግነዋል። ይህም ወንድማማች ህዝቦችን መለያየት እንደማይቻል ያመለከተ እንደሆነ ጠቅስው የክልሉ መንግስት ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ የሚያደርገውን ሁለተናዊ ጥረት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። ህብረተሰቡ በተሳሳቱ አስተሳሰቦች በሚፈፀሙ ጥፋቶች ሳይደናገጥ የብሄረሰቦች መናሃሪያ የሆነውን የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ አንድነቱን ይበልጥ ለማስጠበቅ እንዲረባረብ ጠይቀዋል። የምክር ቤቱ ያልተማከለ የወረዳና የቀበሌ አስተዳደርን ለማጠናከርና በክልሉ በየዕርከኑ የምክር ቤት አባላትን ቁጥር መወሰኛ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይተው በሙሉ ድምፅ አፅድቋል። በዚሁ መሰረት ከማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ የተውጣጡ አስራ አንድ ቀበሌዎችን የያዘ ኡንዱሉ የተባለ አዲስ 21ኛ ወረዳ እንዲዋቀር የቀረበውን ጥናትም ምክር ቤቱ ተቀብሏል። 470 የነበረውን የክልሉን የገጠር ቀበሌዎች ከህብረተሰቡ ባህልና እሴት እንዲሁም የመልማት ጥያቄን መሰረት በማድረግ 48 ተጨማሪ ቀበሌዎችን በማዋቀር 518 እንዲሆኑም ወስኗል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ዋና ኦዲት ቢሮ እና የምክር ቤቱ ፅህፈት ቤት የስድስት ወራት የስራ አፈጻፀም ሪፖርትም በጊዜ መጣበብ ምክንያት ሊቀርብ እንዳልቻለ የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ሀብታሙ ታየ ገልጸዋል። በቀጣይ እነዚህንና ሌሎችን ጉዳዮች የሚያካክስ አስቸኳይ ጉባኤ እንደ አስፈላጊነቱ ሊጠራ እንደሚችልም አፈ-ጉባኤው አመላክተዋል። እስከ ጥር 13 /2012 በሚቀጥለው በዚሁ ጉባኤ በርዕሰ መስተዳድሩ ሪፖርት ላይ ከሚደረግ ውይይት በተጨማሪ የ2012 ተጨማሪ በጀትና የአንድ የምክር ቤት አባልን ቀደም ሲል የተነሳ ያለመከሰስ መብትን የማስመለስ ውሳኔ እንደሚታይም ከወጣው ፕሮግራም ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም