በከተሞች የህብረተሰቡ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ

54
ጅማ ሰኔ 18/2010 በከተሞች ታማኝነትና ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ፡፡ "የህዝብ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ከተማ ለህዳሴችን " በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የኦሮሚያ ከተሞች ፎረም ዛሬ በጅማ ከተማ  ተጀምሯል፡፡ በፎረሙ መክፈቻ ስነስርዓት ወቅት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝደንት ወይዘሮ ጦይባ ሀሰን ባደረጉት ንግግር" ተደራሽነትና ጥራት ያለው መሰረተ ልማትን በከተሞች በማስፋፋት ህብረተሰባችንን ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት መስራት አለብን "ብለዋል፡ በከተሞች በቃት፣ ቁርጠኝነት እና ህዝባዊ  ተቆርቋሪነት ያለው መሪ  በማፍራት የተሻለ ለውጥ ለማምጣት የክልሉ መንግስት እያከናወነ ያለውን ስራ ነዋሪዎችም በመደገፍ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ታማኝነትና ፈጣን አገልግሎት  የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ ለተፈጻሚነቱ ከተሞችን እርስ በርስ በማቀራረብ ልምድ እንዲለዋወጡ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ቤቶችና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው  ቀልጣፋና ግልጸኝነት ያለው አገልግሎት  በከተሞች  ለማረጋገጥና የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት ፎረሙ መቀራረብ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡ "በከተሞች በስፋት የሚታየውን  የኪራይ ስበሳቢነት አመለካከት ችግር ከመሰረቱ በማጥፋት የህብረተሰብን ፍላጎት ለማሟላት ፎረሙ ከተሞች  ልምድ መለዋወጥ አለባቸው" ብለዋል፡፡ በከተሞች የሚታዩ የስራ አጥነት ፣ የመኖሪያ ቤትና የኑሮ ውድነት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመቀነስ መረባረብም አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በፎርሙ ከተሳተፉት መካከል ከነቀምት ከተማ የመጡት  አቶ አያና በሪሶ  በሰጡት አስተያየት"  ፎረሙ የውድድር ስሜትን የሚፈጥር ስለሆነ ለከተሞች እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል" ብለዋል፡፡ በጅማ ከተማ እስከ ሰኔ 22/2010ዓ.ም. በሚቆየው ፎረም  ከሁሉም የኦሮሚያ ከተሞች እንዲሁም ለጅማ አጎራባች ከሆኑት ተርጫ፣ ቦንጋና ወልቂጤ ከተሞች የተወጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም