አገር አቀፍ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የመክፈቻ ፕሮግራም በአዳማ ተካሄደ

59
አዳማ ሰኔ 18/2010 በዘንድሮ የክረምት ወራት ወጣቶች የሚያካሂዱት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የ2010 ዓ.ም አገር አቀፍ የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የመክፈቻ ፕሮግራም ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል። በመርሃ ግብሩ ከ13 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችን ለማሳተፍ  ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል። በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳ እንዳስታወቁት ወጣቶች ለማህበረሰባቸው የሚሰጡት አገልግሎት በጥራት፣ በመጠንና በሽፋን እንዲያድግ ይፈለጋል። ይህንን እውን ለማድረግና ወጣቶች ዕውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ለማህበረሰቡ ግልጋሎት እንዲያውሉ የሚያስችሉ የአሰራር ማዕቀፎችን በመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። ባለፉት 10 ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአገሪቱ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስኮች ላይ በመሰማራት ማህበረሰቡን ከማገልገል ባለፈ ለልማቱ በመንግስትና በህብረተሰቡ የሚደረገውን ከፍተኛ ወጪ ማዳናቸውን ገልፀዋል፡፡ በዘንድሮው የክረምት ወራትም የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመላው የሀገሪቱ ወጣቶች በተፈጠረው የለውጥና የሀገር ወዳድነት ስሜት ታጅቦና ቅንጅታዊ አሰራርን ተከትሎ ከ14 በላይ የሆኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል። ፕሮግራሙ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በሚሰማሩበት አካባቢዎች ከአቻዎቻቸውና ከማህበረሰቡ ጋር መልካም ትስስርና መቀራረብ እንዲያዳብሩ ዕድል የሚፈጥርላቸው በመሆኑ ለስኬቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ አቶ ርስቱ አሳስበዋል። ኢትዮጵያዊያን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያላቸውን ድጋፍና ፍቅር ለመግለጽ ሰላማዊ ሰልፍ በወጡት ላይ ፀረ ሰላም ሃይሎች የፈጸሙትን እኩይ ተግባር በመላው የሀገሪቱ ወጣቶችና የስፖርት ቤተሰቦች ስም አውግዘዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወጣት ታረቀኝ አብዱልጀባር በበኩሉ የዘንድሮ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር የሚካሄደው “የተቀናጀ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሁለንተናዊ ልማትና ሰላም እሴቶች ግንባታ” በሚል መሪ ቃል መሆኑን ገልጿል። በመርሃ ግብሩ ላይ 13 ነጥብ 8 ሚሊዮን ወጣቶችን ለማሳተፍ ፌዴሬሽኑ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ትውልድ የሚገነባበት፣ ወጣቶች ልምዳቸውንና እውቀታቸውን ለሌሎች የሚያስተላልፉበት እንዲሁም ያሉባቸውን ጉድለቶች የምንሞላበት ይሆናል ብሏል። ሰኔ 16ቀን 2010 በአዲስ አበባ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመደገፍ አደባባይ በወጡ ሰላማዊ ዜጎች ላይ በተፈጸመ የቦንብ ጥቃት ፌዴሬሽኑ እጅግ ማዘኑንና የደረሰውንም ጥቃት እንደሚያወግዝ ወጣት ታረቀኝ አስታውቋል። በእነዚህ ንፁሃን ዜጎች ላይ በደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ላጋጠመው የደም እጥረት በዛሬው የወጣቶች በጎ ፈቃድ መክፈቻ ላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ከ100 የሚበልጡ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት ደም ለግሰዋል። ከደም ለጋሾች መካከል የአዲስ አበባ ነዋሪ ወጣት ፋኑኤል አበራ በሰጠው አስተያየት ለሁለተኛ ጊዜ ደም መለገሱን ገልፆ በዚህ ሰብዓዊ ተግባር በመሳተፌ ደስተኛ ነኝ ብሏል። የጋምቤላ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኮንግ ጃክ በበኩላቸው ደም ልገሳ የሰው ሕይወት ማዳን እሰከሆነ ድረስ ወጣቶች መስራት ካለባቸው ስራዎች ውስጥ በቀዳሚነት ሊፈጽሙት ይገባል ብለዋል። ደም መለገስ ሕይወትን ማዳን ስለሆነ በደም እጦት ለጉዳት የሚዳረጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመታደግ ደም መለገሱን የተናገሩት ደግሞ በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ማቲያስ አሰፋ ናቸው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም