ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ቀንበር አለመውደቋ ባህላዊና ኃይማኖታዊ ስርዓቷ ሳይበረዝ እንዲቆይ አስችሏል

102
አዲስ አበባ ጥር 11 ቀን 2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር አለመውደቋ ባህላዊና ኃይማኖታዊ ስርዓቷ ሳይበረዝ እንዲቆይ ማስቻሉን ባሕረ ጥምቀት የታደሙ የውጭ አገራት ጎብኚዎች ተናገሩ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አስተምህሮ መሰረት በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበረው የጥምቀት በዓል ዛሬም የእምነቱ ተከታይ ምዕመናን ባሉበት በመላ አገሪቷ በድምቀት ተከብሯል። በዓለም የማይዳሰስ ወካይ ቅርስነት መዝገብ የሰፈረው የጥምቀት በዓል በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ላይ በርካታ የውጭ አገራት ጎብኚዎች ተሳትፈዋል። በአደባባይ ከሚከወኑ በዓላት መካከል አንዱ በሆነው የጥምቀት ክብረ በዓል መታደማቸው በከፍተኛ ደረጃ እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል ጎብኚዎቹ። የበዓሉ አከባበር የኢትዮጵያን የረጂም ጊዜ ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መንገድ መከበሩ፣ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻቸው ለትውልድ ማስተላለፍ በመቻላቸው የተሻገረ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ የስዊዲን አምባሳደር ቶርብዮርን ፔተርሰንን ጨምሮ ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት ኢትዮጵያ የከተሙ እንግዶች ኢትዮጵያ እንደ ጥምቀት አይነት ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ጎልተው የሚወጡበት ክብረ በዓል መሆኑን ተናግረዋል። በክብረ በዓላት የሚከወኑ ትውፊታዊ ስርዓቶች ለዘመናት ሳይበረዙ የመቆየታቸው ምስጢር አንዱ ምክንያት ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ቀንበር ሳትወድቅ በሉዓላዊነት ለዘመናት መኖሯ እንደሆነም ይናገራሉ።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም