'የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የሰላም አምባሳደሮች ሆኖው መስራት አለባቸው'-ፕሮፌሰር ክንደያ

90
መቀሌ ጥር 11 ቀን 2012 (ኢዜአ ) በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የሰላም አምባሳደሮች መሆን እንደሚጠበቅባቸው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት አሳሰቡ። በመቀሌ ከተማ ልዩ ስሙ አይናለም እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ነዋሪዎች ለዩኒቨርሲቲው ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎች የጥምቀት በዓልን አስመልክተው ዛሬ የምሳ ግብዣ  አድርገዋል። ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት በዚህ ወቅት ተማሪዎቹ የሰላም አምባሳደሮች በመሆን ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል። የትግራይ ክልል ሰላሙን ያረጋገጠበት ምስጢር በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የሚገኘው ሕዝብና ዩኒቨርሲቲዎች ለሰላም ዋጋ ሰጥተው ዘብ በመቆማቸው ነው ብለዋል። በየደረጃው በሚደረገው እንቅስቀሴ የክልሉ ሰላም ማረጋገጥ ተችሏል ያሉት ፕሮፌሰር ክንደያ፣የሁሉም ክልሎች ዘላቂ ሰላምና ልማት የሚረጋገጠው ግን እያንዳንዱ የተቋማቱ ተማሪ የሰላም አምባሳደር ሲሆን ነው ብለዋል። በመሆኑም ሁሉም የተቋማቱ ተማሪዎች ለዚህ በጎ ተግባር አምባሳደሮች ለመሆን  ኃላፊነት ወስደው በትጋት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ፕሬዚዳንቱ አስገንዝበዋል። የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ካሳሁን ሙሉ በበኩላቸው በዓሉን ስናከብር ሰላም፣ፍቅርና አንድነትን አጠናክረን የምናስቀጥልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ወጣት አብረሀላይ አራፋይኔ በዓሉን  አስመልከተው ግብዣውን ላዘጋጁት የአይናለም ማህበረሰብ አባላት  ምስጋናውን አቅርቧል። ከግብዣው ተሳታፊዎች መካከል ከአማራ ክልል ደብረማርቆስ ከተማ የመጣ የዩኒቨርሲቲው አንደኛ ዓመት ተማሪ ወንድምነህ መከተ በዓሉን በፍቅርና በአንድነት በማክበሩ ደስታ ተሰምቶኛል ብሏል። ወጣቶች ከሁከትና ግርግር ራሳቸውን ነፃ በማድረግ በሰላም እንዲኖሩ መልዕክቱን አስተላልፏል። ከደቡብ ክልል የመጣውና የዩኒቨርሲቲው የሶስተኛ ዓመት ኬሚካል ኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍል ተማሪ ገዛኽኝ ተካ በዓሉን ለቱሪስት መስሀብነት ለማስተዋወቅና የገቢ ምንጭ ለማድረግ እንሰራለን ብሏል። የአይናለም  ቀበሌ ማህበረሰብ ተወካይ አቶ እያሱ ፃዲቅ ማንኛውም ተማሪ ማህረሰቡን እንደ ቤተሰቡ በዓሉንም ልክ በቤቱ እንደሚያከብረው አስቦ በፍቅር እንዲያሳልፍ ፍላጎታቸው መሆኑን ተናግረዋል። ተማሪዎቹ ሰላማቸውን አስጠብቀው የመማር ማስተማር ስራቸውን እንዲያከናወኑ አሳስበዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም