የዓለም ቅርስ የሆነውን የጥምቀት በዓል ቅርስነት መጠበቅ የሁሉም ሃላፊነት ነው

66
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 11/2012   በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበውን የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ትሁፊቱንና መገለጫዎቹን በዘላቂነት መጠበቅ የሁሉም ሃላፊነት እንደሆነ ተጠቆመ። የጥምቀት በዓል በአለም የትምህርት፣ሳይንስና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት በዚህ አመት መመዝገቡ ይታወሳል። በዓሉ በቅርስነት መመዝገቡ ከኢትዮጵያ አልፎ የአለም ቅርስ መሆኑን እንደሚያሳይ ነው አስተያየት ሰጪዎች የተናገሩት። የጥምቀትን በአል ለመታደም ከተለያዩ የአለም አገራት ይመጡ የነበሩ ጎብኝዎችን ቁጥርም ይጨምራል የሚል እምነት አላቸው። በዚህም ኢትዮጵያ ያላትን እሴትና ባህል ለአለም በማስተዋወቅ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፉ ተጠቃሚ ትሆናለች። ነገር ግን ይህንን የማይዳሰስ ቅርስ ተብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍና ለአለም ለማስተዋወቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት አለበት ብለዋል። የእምነቱ ተከታዮችም በበአሉ ወቅት የሚከወኑ ሁነቶችን ከአለባበስ ጀምሮ ሃይማኖታዊ ትሁፊቱን በመጠበቅ ለአለም በማስተዋወቅ ቅርሱን መጠበቅ ይገባቸዋል ብለዋል። የጥምቀት በአል ሃይማኖታዊና ማህላዊ እሴቱን ይዞ እንዲቀጥል ሁላችንም ሃላፊነት አለብን ብለዋል። በዩኔስኮ አዲስ አበባ ላይዘን ኦፊስ የባህል መርሃ ግብር ባለሙያ አቶ ጌቱ አሰፋ ዩኔስኮ ቅርሶችን በአለም ቅርስነት ሲመዘግብ ዋና አላማው ቅርሶችን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ  መሆኑን ይገልጻሉ። እነዚህ ቅርሶች እንዲጠበቁ የሚከበርበት ቦታ፣ በበአሉ የሚዘወተሩ አልባሳትና እውቀት መኖሩም ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል። አገራት ቅርሶችን ሲያስመዘግቡ ጠብቀው ለትውልድ ለማስተላለፍ በሚገቡት ቃል መሰረት ይህንን ለማድረግ ዩኔስኮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው የጨመሩት። ይሁን እንጂ ቅርሱን ለመጠበቅ ትልቁ ሃላፊነት የህዝብና የመንግስት እንደሚሆን ነው የተናገሩት።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም