የባህል አልባሳትና የጸጉር አሰራር ልማድ ለጎንደር የጥምቀት በዓል ተጨማሪ ድምቀት ፈጥሯል

159
ጎንደር (ኢዜአ) ጥር 11/2012 የጎንደርና አካባቢው መገለጫ የሆኑት የቀደመ የአለባበስና የፀጉርቨ አሰራር በወጣቱ ዘንድ እየተዘወተረ መምጣቱን ባህሉ እንዳይረሳና እንዳይጠፋ እየሆነ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ። ወጣቱ ትውልድ ባህሉን ለመጠበቅ እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ ለቱሪዝም እድገቱ ወሳኝ ድርሻ ያበረክታል ሲል የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ አስካል እንዳለ ለኢዜአ እንደተናገሩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣቱ የጎንደር መገለጫ ያልሆኑ አልባሳትን ለጥምቀት ሲያዘወትር በመመልከታቸው ያዝኑ እንደነበር አስታውሰዋል። በተለይም ሴቶች መጤ ባህል የሆነ የአለባበስና የፀጉር አሰራር ሲከተሉ ባህሉ ሊጠፋ ነው የሚል ስጋት ፈጥሮባቸው እንደነበረም ገልጸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣቶች ወደ ቀደመውና ማራኪ ባህል መመለሳቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። የጎንደርና አካባቢውን ባህላዊ ቀሚስ የሃገሬው ሰው ብቻ ሳይሆን የውጭ ጎብኝዎችም ጭምር በመልበስ እያጌጡበት መምጣቱንም ተናግረዋል። የጎንደር ቀሚስ ከኋደኞቿ ጋር ስትገዛ ያገኘናት ወጣት ህሊና ዳኛቸው በበኩሏ ከዚህ ቀደም የባህል ልብስ ገዝቶ የመልበስ ፍላጎት እንዳልነበራት ጠቅሳለች። አሁን ላይ ግን ባህል ተጠብቆ የሚዘልቀው በወጣቱ ዘንድ መሆኑን በመረዳት የዚህን ዓመት የጥምቀት በዓል በጎንደር ቀሚስ ደምቃ ለመዋል መወሰኗን ገልፃለች። በተለምዶ አራዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሀገርኛ ልብሶች ነጋዴ የሆኑት አቶ ተፈራ ጌጡ በበኩላቸው በዚህ አመት በተለይም የጎንደር ቀሚስ በስፋት እየተሸጠላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በገበያው ተጠቃሚ ከመሆናችን ባሻገር አዲሱ ትውልድ ባህሉን ለመጠበቅ ከውጭ አልባሳት ጥገኝነት መውጣቱ ትልቅ እድል”ነው ነው ያሉት ነጋዴው ከወጣቶች በተጨማሪ ወላጆች ለህፃናት ልጆቻቸው በስፋት እየገዙ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በፋሲል ክፍለ ከተማ በሴቶች የውበት ሳሎን ሙያ የምትሰራው ወጣት ኤልሳ ወርቁ በበኩሏ ከጥምቀት በዓል ጋር በተያያዘ የጎንደር ሹርባ የሚሰሩ ደንበኞች ቁጥር በመበራከቱ ሁለት ተጨማሪ ሰራተኞችን ቀጥራ እያሰራች እንደሆነ ገልፃለች። “ብዙ ሴቶች ሹርባ ለመሰራት ስለሚመጡ ወረፋ ለሶስት ቀን ያክል ይዘው የሄዱ አሉ” ያለችው ወጣቷ ስራው ጥሩ ገቢ እንዳለውና ከኤሌክትሪክ ፍጆታም እንደሚታደጋት ገልፃለች። በጎንደር ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም መመሪያ ኃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ በበኩላቸው “የጎንደርና አከላባቢው ባህላዊ አለባበስና የፀጉር አሰራር ለቱሪዝም እድገቱ አወንታዊ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው”ብለዋል። “ከውጭ የሚመጡ ቱሪስቶች የተለየ ነገር ማየት ይፈልጋሉ” ያሉት ኃላፊው ባህላዊ አለባበሶችና ክዋኔዎች ለቱሪስቶች የተለየ ደስታን በመፍጠር ሌሎችን እንዲስቡ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ጎንደር ቅርሶቿና በድርሳናት የተቀመጡ ታሪኮቿ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ባህላዊ ክዋኔዎቿም ትልቅ የቱሪስት መስህብ ሀብቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ወጣቶቹ ይህንኑ ባህልና ወግ ማስቀጠል መቻል እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። በወጣቱ ዘንድ እየተስተዋለ ያለውን ባህልን ጠብቆ የመጓዝ መነቃቃት አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል። የጎንደርና አካባቢው መገለጫ የሆነው የጥምቀት በዓል የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገራት ጎብኚዎችና የዕምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በድምቀጥ እየተከበረ ይገኛል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም