ከቂምና ጥላቻ በመራቅ ሃገራዊ ፍቅርና አንድነትን ማጠናከር ይገባል…ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ

111
ጎንደር ጥር 10/2012  (ኢዜአ) በጠንካራ ሃገራዊ ፍቅር በመተሳሰር አንድነትን ማምጣትና ጥላቻንና ቂም በቀልን ማስወድ ይገባል ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ጥሪ አቀረቡ። በጎንደር ከተማ እየተከበረ ባለው የጥምቀት በዓል ብፅዑነታቸው የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ-ስብከት ፀሐፊ መላከ ምህረት አምሃ መኳንንት በኩል ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት የዘመኑን የመለያየትና የክፋት አስተሳሰብ በፍቅርና በትዕግስት በማለፍ አንድ መሆን ያስፈልጋል። በመካከላችን የሚሰማውን ቂምና የበደል እዳ በመሰረዝ ከዘረኝነት፣ ባርነት ነፃ መውጣትና አንድነታችንን ከንግግር ባለፈ በተግባር ማሳየት ይገባልም ብለዋል። ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከአባቶቹ የወረሰውን አንድነትንና ስነ-ምግባርን በተግባር ማሳየት እንደሚገባም ነው ብፅዕነታቸው በመልዕክታቸው ያስተላለፉት፡፡ እየተከበረ ያለው የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያውያን መካከል ፍቅርን የሚያመጣ እንደሆነ አመልክተዋል። “በቀደምት ታሪክ ያልነበረና ያልተለመደ መጤ ልምድ የሆነው ወገንን መበደልና የእምነት ተቋማትን ማቃጠልን በማስቀረት ሁሉም በሃገራዊ ሃላፊነት ሊሰራ ይገባል” ብለዋል። "ትዕግስትን ከፈጣሪ ልንማር ይገባል" ያሉት ብፁእነታቸው ህዝበ ክርስቲያኑ የቤተ ክርስቲያኗን ታሪክና ልዕልና በሚመጠን ተግባር መሳተፍ እንደሚገባውም ገልፀዋል። “በመላው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው የጥምቀት በዓል በዩኒስኮ በማይዳስስ ቅርስ በማስመዝገብ ዘመኑ ኢትዮጵያ በአለም ከፍ ብላ የታየችበት ወቅት ነው” ብለዋል። በመሆኑም መላው የተዋህዶ ልጆች የጥምቀት በዓልን ሲያከብሩም አንድነትንና ፍቅርን በሚገዛ አግባብ መሆን እንዳለበትም በተወካያቸው ባስተላለፉት መልዕክት አሳስበዋል። የዘንድሮው የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች አንዲሁም የሃገር ውስጥና የውጭ ሀገራት እንግዶች በተገኙበት በሰላማዊ መንገድ እየተከበረ ይገኛል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም