የጥምቀት በዓል በምሥራቅ ወለጋ ዞን ተከበረ

132
ነቀምቴ ጥር 11 ቀን 2012 ኢ ዜ አ  የጥምቀት በዓል በነቀምቴ ከተማና በምሥራቅ ወለጋ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች መከበሩን የዞኑ አስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ገለጸ። ጽህፈት ቤቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው በዓሉ በዞኑ ርዕሰ ከተማና በ17 ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ ከተሞች ያለምንም የፀጥታ ችግር እየተከበረ ነው። የነቀምቴ ከተማ ነዋሪው  አቶ ያሬድ ባሻዬ በዓሉ የባህል መሠረቱን ባስጠበቀ፣ መቻቻልና መከባበርን መሠረት ባደረገ መልኩ በሰላምና በደስታ እያከበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ። የከተማው 06 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እናት ወርቁ  በዓሉን በጥሩ መንፈስ እያከበሩት መሆናቸውና በዓሉ በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት በመመዝገቡ ደስታቸውን እጥፍ ድርብ እንዳደረገው ገልጸዋል። አቶ ዶክተር ሞሲሳ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በዓሉን በሰላም በማከበር ላይ  መሆናቸውን ይናገራሉ። ሆኖም በአገሪቱ ለዘመናት የተጠበቀውን የሐይማኖት መቻቻልና ተከባብሮ የመኖር ባህልን ማጠናከርና አንድነትን ማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል። ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምሀርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት በማይዳሰስ ቅርስነት ከተመዘገበ ወዲህ የመጀመሪያውን የጥምቀት በዓል ዛሬ እያከበረች ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም