በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ300 መቶ ሺህ ብር በላይ ያጭበረበሩ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

62
አሶሳ  ሰኔ 18/2010  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሃሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ከ300 መቶ ሺህ ብር በላይ ያጭበረበሩ ሁለት ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ። በእስራት የተቀጡት ግለሰቦች በክልሉ ድባጤ ወረዳ ብድርና ቁጠባ ተቋም ገንዘብ ያዥ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች ናቸው። ግለሰቦቹ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑ ደንበኞች ገቢ የሚሰበስቡባቸው ደረሰኞች ላይ የተመዘገቡ የገንዘብ መጠኖችን ሰርዘው በመቀየር እንዲሁም ሃሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት በፈፀሙት የማጭርበር ተግባር በእስራት ተቀጥተዋል። የክልሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት  ዳይሬክተር አቶ አማረ መኩሪያ እንደገለጹት ግለሰቦቹ ወንጀሉን የፈፀሙት ከ2008 እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ በወረዳው የብድርና ቁጠባ ተቋም ባልደረባ ሆነው ሲሰሩ ነው፡፡ የኮሚሽኑ አቃቤ ህግ ባደረገው ምርመራ በድባጤ ወረዳ ብድርና ቁጠባ ተቋም ገንዘብ ያዥ የነበረችው ወይዘሮ እልልተወርቅ አዳሙ ከሁለት መቶ 17 ሺህ ብር በላይ እንዲሁም አቶ ሃብታሙ ጅባታ ከ91 ሺህ ብር በላይ የገቢ ደረሰኞችን በመሰረዝና ሀሰተኛ ደረሰኝ በመጠቀም ማጭበርበራቸው ሊረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ግለሰቦቹ በፈጸሙት የማጭርበር ተግባርም ከ309 ሺህ ብር በላይ የመንግስትና የህዝብ ሃብት ላይ የሙስና ተግባር መፈጸማቸውን አቶ አማረ ገልፀዋል፡፡ ጉዳዩን ሲመረምር የነበረው የመተከል ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ሰኔ 6 ቀን 2010 ዓ.ም በዋለው ችሎት ወይዘሮ እልልተወርቅ አዳሙን በሦስት ዓመት እንዲሁም አቶ ሃብታሙ ጅባታን በሁለት ዓመት ጽኑ እስራ እንዲቀጡ ወስኗል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም