ጥምቀትን የትኞቹ አገሮች በተቀራራቢ ቀናት አከበሩ?

90
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 11/2012 ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የክርስትና ኃይማኖት ተከታይ የዓለም አገራት የጥምቀት በዓልን በጥር ወር እያከበሩ ይገኛሉ። ዛሬ የጥምቀት በዓልን እያከበሩ ከሚገኙ የዓለም አገራት መካከል አንዷ ህንድ ናት። በሕንድ የሚኖሩ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በዓሉን በድምቀት አክብረዋል። የበዓሉ ገጽታ በከፊል እንደሚያሳየውም ባልካናዊቷ አገር ቡልጋሪያም ከቅርብ ወራት አንስታ በዓሉን እያከበረች ትገኛለች። ቡልጋሪያውያን በዚህች ዕለት በበረዶ ውሃ ውስጥ ገብተው በመደነስና በመደሰት ያሳልፉታል። ምንም እንኳን ወንዶች ብቻ ወንዝ ውስጥ እንዲገቡ ቢፈቀድም፤ ይህ የሚደረገው ደግሞ መልካም ጤናን ለመላበስ የሚደረግ መሆኑም ታምኖበት ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ሌሎች ኃይማኖታዊ ክንውኖችም ይደረጋሉ። የቱርክ የግሪክ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችም በዓሉ ላይ ሲሳተፉ በጳጳሱ ወደ በረዷማ ውኃ የሚወረወረውን ከእንጨት የተሰራ ምልክት ለመፈለግ ወንዶች ወደ ቀዝቃዛው ውሃ ዘለው በመግባት  ይፈልጋሉ። መስቀሉን ቀድሞ ያገኘ ሰው ከእርኩስ መንስፈስ ይርቃል፤ ዓመቱን ሙሉ ጤነኛ ይሆናል ተብሎም ይታመናል። የሩሲያ ኦርቶዶክስ አማኞችን ስንመለከት ደግሞ ሩሲያውያን የእየሱስ ክርስቶስን መጠመቅ ለማሰብ ሶስት ጊዜ በረዷማ ውሃ ውስጥ ሰጥመው በመውጣት በዓሉን ያከብሩታል። የእምነቱ ተከታዮች ከባዱ ቀዝቃማ አየር ሳይበግራቸው ኃይማኖታዊ ስርዓቱን ያከናውናሉ፤ በዓሉንም ያደምቁታል። ስፔንን ስንመለከት ደግሞ ሕጻናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ከተሞች ጫፍ በሚያደርጉት የእግር ጉዞ ድምቅ ብሎ ይከበራል። ከዚሁ ጋር ታይይዞ በስፔናውያን ስጦታ የመሰጣጣት ልምድም በስፋት ይዘወተራል በጥምቀት። በግሪክ፣ በአውስትራሊያ፣ በሜክሲኮም በዋናነት የጥምቀተ ባህሩ ተግባር የሚከናወን ቢሆንም እንደየ ልዳቸውና ባህላቸው የተለያዩ ክንውኖች በዓሉን ያስውቡታል። ለምሳሌ በሜክሲኮ ኬክ በተለያየ ቅርጽ ተዘጋጅቶ በስጦታ መልክ ለህጻናት ይበረከታሉ። በአጠቃላይ የክርስትና እምነት ተከታዮች ባሉባቸው አገራት ሁሉ የእየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል የተለያዩ ገጽታዎች ተላብሶ ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል። ኢትዮጵያም ዛሬ በተለየ ድምቀት እክብረዋለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም