በምዕራብ ሐረርጌና በኢሉአባቦር ዞኖች በክረምቱ ከ257 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እየተተከሉ ነው

67
ጭሮ/መቱ ሰኔ18/2010 በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በክረምቱ 166 ሚሊዮን የተለያዩ ችግኞች ተከላ መጀመሩን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ። በኢሉአባቦር ዞንም ከ23 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ የተራቆተ መሬት ላይ የተለያዩ የዛፍ ችግኞች ተከላ ሥራ መጀመሩም ተመልክቷል። በምዕራብ ሐረርጌ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት  የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማት ቡድን መሪ አቶ መኮንን ተፈራ እንዳሉት የችግኝ ተከላ ሥራው በ11 ወረዳዎች እየተካሄደ ያለው ከሰኔ 1 ቀን 2010 ጀምሮ ነው። እስከ መጪው ሐምሌ ወር አጋማሽ በሚቆየው በእዚህ የችግኝ ተከላ ሥራ ላይ 476 ሺህ 877 ሄክታር  የተራቆተ መሬት ለማልማት ታቅዷል። በችግኝ ተከላ ሥራው አርሶ አደሮች፣ ተማሪዎችና ወጣቶች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም ከ49 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል መቻሉን አቶ መኮንን ገልጸዋል። በብዛት በመተከል ላይ ከሚገኙት አገር በቀል የዛፍ ዝርያዎች መካከል ጥድ፣ ሸውሸዌ፣ ወይራ፣ ባህር ዛፍና የተለያዩ የመኖ ችግኞች ይገኙበታል። በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በዶባ ወረዳ ሀደስ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ያሲን አሊዩ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ዓመታት በተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል በአሁኑ ወቅት በችግኝ ተከላው እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል። "በበጋና በክረምት ወራት በራሳችን ፍላጎትና ተነሳሽነት በተፋሰስ ልማትና ችግኝ ተከላ መሳተፋችን በግብርና ሥራችን ተጠቃሚ እያደረገን በመሆኑ በቀጣይም አጠናክረን እንቀጥላለን" ብልዋል። ቀደም ባሉ ጊዜያት የተከሏቸው ችግኞች የእርሻ መሬቱን ለምነት ከመጠበቅና የአፈር መሸርሸርን ከመከላከል ባሻገር ለእንስሳት መኖም እያገለገላቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ዩሱፍ ኡመሬ ናቸው፡፡ "አርሶ አደር ወንድይፍራው ደበበ በበኩላቸው በየዓመቱ ችግኝ በመትከላችንና በመንከባከባችን የተጎዱ ተፋሰሶች አገግመዋል" ብለዋል ። በበጋ ወቅት የወንዞችና ምንጮች ውሃ የማመንጨት አቅማቸው እየጎለበተ በመምጣቱ ለመስኖ ልማት ሥራው ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡ በዘንድሮው ዓመትም በርካታ ችግኝ ተረክበው በአሁኑ ወቅት በእርሻ ማሳቸው ዳርቻ በመትከል ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተመሳሳይ ዜና በኢሉአባቦር ዞን በበጋው ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የተካሄደባቸውን ጨምሮ ከ23 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ የተራቆተ መሬት ላይ የችግኝ ተከላ መጀመሩን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌቱ ለገሰ እንደገለጹት ከተያዘው ሰኔ ወር ጀምሮ ከ91 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የደን ችግኞች እየተተከሉ ያሉት በተለያዩ ምክንያቶች በተራቆቱ አካባቢዎች ላይ ነው፡፡ በችግኝ ተከላ ሥራው በዞኑ 11 ወረዳዎች የሚገኙ ከ200 ሺህ በላይ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በጋራና በተናጠል በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ አቶ ጌቱ እንዳሉት በአንድ ሳምንት ግዜ ውስጥ ከ1ሺህ 100 ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ የዛፍ ችግኞች ተተክለዋል፡፡ በዞኑ አሌ ወረዳ ገርበዲማ ቀበሌ አርሶአደር እንዳለ ሽፈራው በሰጡት አስተያየት በየዓመቱ እየተተከሉ ያሉ የዛፍ ችግኞች የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ "የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤም ይሁን የችግኝ ተከላ ሥራ ጥቅሙ ለራሳችን ስለሆነ በተነሳሽነት ነው የምንሰራው” ያሉት አርሶአደሩ፣ በቡድን በልማቱ መሳተፋቸው የበለጠ ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በማሳቸው ዳርቻ የእንስሳት መኖ በመትከል ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በሁሩሙ ወረዳ ቶማ ዮቢ ቀበሌ አርሶአደር ነጎ ቢራቱ ናቸው፡፡ የእንስሳት መኖ ተክለው ለከብቶቻቸው ቀለብ ማዋላቸው እንስሶቻቸው በቂ መኖ እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡ ዘንድሮም አንድ ሄክታር ማሳ ላይ በሰሩት እርከን ዳርቻ የሳር መኖዎቹን በመትከል ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት እያደረጉ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ በኢሉአባቦር ዞን ባለፈው ዓመት ከተተከሉት ከ130 ሚሊዮን የዛፍ ችግኞች ውስጥ ከ88 ከመቶ በላይ የሚሆኑት መጽደቃቸውን ከዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል ።                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም