የሴቶችና ህፃናት መብትና ደህንነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ ርብርብ ያስፈልጋል

155
አዳማ ሰኔ18/2010 የሴቶችን እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ የተቀናጀ ርብርብ እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ። በሴቶችና ህጻናት ላይ የተከናወኑ ሥራዎችን በመገምገም በቀጣይ የተግባር አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ የሁለት ቀናት ዓውደ ጥናት በአዳማ ከተማ ተካሔዷል። የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ፀጋይ በዓውደ ጥናቱ መክፈቻ እንደተናገሩት መንግስት ሴቶችን በሁሉም የልማት መስኮች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግና የህፃነት መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ በወሰዳቸው ተቋማዊ እርምጃዎች ለውጥ ተመዝግቧል። ይሁን እንጂ በአስፈጻሚ አካላትና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የተመዘገበው ውጤት በሚፈለገው መጠን አለመሆኑን አመልክተዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እሙዬ ቢተው በበኩላቸው እንደገለፁት ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው የክትትልና የድጋፍ ሥራ ሴቶችና ህጻናት አስመልክቶ በአስፈጻሚ አካላት ላይ የሚታዩ በርካታ ክፍተቶች መኖራቸው ተረጋግጧል። በመድረኩ ላይ ባቀረቡት የክትትልና የቁጥጥር ግኝትም አቅመ ደካማ ሴቶች መሬታቸውን አለአግባብ ሲነጠቁ የህግ ድጋፍ እንደማያገኙ ፣ በማህበር የሚደራጁ ሴቶች በቂ የመስሪያ ቦታና የገበያ ትስስር እገዛ እንደማይደረግላቸው ነው የገለጹት። በተጨማሪም ሴቶች ባፈሩት ሀብት እኩል የንብረት ክፍፍል እንደማያገኙና ለእኩል ሥራ እኩል ተጠቃሚ ያልሆኑበት አጋጣሚ በርካታ መሆኑን በማሳያነት አቅርበዋል። አንዳንድ ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናት መሬታቸውን አለአግባብ እንደሚወሰድባቸውና የህግ ድጋፍ እንደማያገኙ እንዲሁም ለጉልበት ብዝበዛ እንደሚዳረጉም አስረድተዋል። እንደ ወይዘሮ እሙዬ ገለጻ በጉዲፈቻ የተወሰዱ ህጻናት የተደራጀ መረጃ አለመኖር፣ ጥቃት የደረሰባቸው ህፃናት በአግባቡ የህግ ድጋፍ እያገኙ አለመሆኑ በድጋፍና ክትትል ሥራ ከተለዩ ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ ። አሁን እየታዩ ያሉት ክፍተቶችን ለመሙላት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ተቀናጅተው ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባም ወይዘሮ እሙዬ አሳስበዋል። የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ የኋላሸት ገብሬ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት "በሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያልተሻገርናቸው በርካታ ክፍተቶች አሉ" ብለዋል። በመሆኑም በዘርፉ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እስከታች ድረስ ወርዶ በቅንጅት ለመስራትና ርብርብ ለማድረግ እንደሚጥሩ አስረድተዋል። መድረኩ ክፍተቶችን በጋራ ገምግሞ ለቀጣይ የተሻለ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሚረዳም አመልክተዋል። በዓውደ ጥናቱ ላይ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የመጡ የዞን የሴቶችና ህፃናት መምሪያ ኃላፊዎች፣ የክልል የቢሮ ኃላፊዎችና ከየሴክተሩ የተወጣጡ 160 ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም