የጤና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሽግግርን ማስፋት ያስፈልጋል

65
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2010 የምስራቅ አፍሪካ ሄልዝ ፌዴሬሽን 7ኛ አመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ የግል ጤና ተቋማት አሰሪዎች ማህበር ገለጸ። ጉባኤውን ኢትዮጵያ ስታዘጋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን “ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለአፍሪካ ጤና ሴክተር ስር ነቀል ለውጥ'' በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው ጉባዔ ከ100 በላይ የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎችና አመራሮች ይሳተፋሉ። ማህበሩ ሐምሌ 2 እና 3 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ የሚካሄደውን ጉባኤ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። ጉባኤው በጤናው ሴክተር ላይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በማስረጽ ፈጣንና ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎትን ለማስፋት እድል የሚፈጥር እንደሆነ ተገልጿል። የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር መኮንን አይችሉም እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ የሚሰጠው የጤና አገልግሎት የዲጂታል ቴክኖሎጂ በሚፈለገው ልክ ተግባራዊ የሆነበት አይደለም። በዚህም የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በሁሉም የጤና ተቋማት በማስረጽ የጤና አገልግሎቱን ፈጣንና ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። በተለይም የግል የጤና ተቋማት ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ያላቸው ሚና የጎላ እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ አክለዋል። የሚካሄደው የጤና ጉባኤ በምስራቅ አፍሪካ አገሮች በግሉ የጤና ዘርፍ የተጀመረውን ቅንጅታዊ አሰራር የሚያጎለብት ከመሆኑም በላይ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተናግረዋል። በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ማነቆዎች በመለየትና ከመንግስት የህክምና ተቋማት ባልተናነሰ መልኩ የግሉም ሴክተር ሊያበረክት ስለሚገባው ተግባር ከሌሎች አገር የተወሰዱ ልምዶችም የሚቀርቡበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል። የምስራቅ አፍሪካ ሄልዝ ኬር ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ዘላለም ፍሰሃ በበኩላቸው በጉባኤው ላይ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ በሜዲካል ሳይንስ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂና እድገትን በመጠቀም ዘርፉን ማዘመን የሚያስችል የአገሮች የተሞክሮ ልውውጥ እንደሚደረግ ጠቁመዋል። ጉባዔው የግሉ ዘርፍ በጤና መሰረተ ልማት ተሳታፊ እንዲሆንና የተካሄዱ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማስቻል የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ዩጋንዳ፣ ኬኒያ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳንና ቡሩንዲ የምስራቅ አፍሪካ ሄልዝ ፌዴሬሽን አባል አገሮች ናቸው። የኢትዮጵያ የግል ጤና ተቋማት አሰሪዎች ማህበር በዘጠኙም የአገሪቱ ክልሎች ከ12 ሺህ በላይ የሚሆኑ የግል ጤና ተቋማትን በስሩ ያቀፈ እንደሆነ ከማህበሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም