ክልሎች ለባህል ማዕከላት መስፋፋት የሰጡት ትኩረት በቂ አይደለም ተባለ

61
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2010 የክልል መንግስታት የብሄር ብሄረሰቦችን ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች ለማሰባሰብ፣ ጠብቆ ለማቆየትና ሳይበረዙ ለትውልድ ለማስተላለፍ ዓይነተኛ መሳሪያ ለሆኑት የባህል ማዕከላት የሰጡት ትኩረት አነስተኛ መሆኑን ባለሙያዎችና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ። በአገሪቱ የማዕከላቱ መስፋፋት የብሄረሰቦችን ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች በጥናትና ምርምር ለማበልፀግ ጭምር መነሻ ሆነው እንደሚያገለግሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎችና እንደራሴዎች ተናግረዋል። ሆኖም ግን ''የክልል መንግስታት ለባህል ማዕከላት ግንባታ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ አይደለም'' ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል። በደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ታሪክ ቅርስ ጥናትና ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መሀመድ አምቢሶ እንደሚሉት፤ በክልሉ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ የባህል ማዕከል ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ ዘጠኝ ዓመታት ተቆጥረዋል። የክልሉን ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ታሪክና ባህል የሚያሳዩ የብሄረሰቦች መንደር፣ የእደ ጥበብና ስነ-ጥበብ ሙዚየምን እንዲያካትት የታሰበው የባህል ማዕከሉ ግንባታ እስካሁን እንዳልተጀመረ ጠቁመዋል። "ማዕከሉ ምን መምሰል እንዳለበት በየጊዜው ልምድ እየተወሰደ የመነሻ ሰነድ ለአመራሮች ቢቀርብም ግንባታው መቼ እንደሚጀመር አይታወቅም" ብለዋል። ይህም የክልሉ አመራሮች ለባህል ማዕከሉ የሰጡት ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑን እንደሚያሳይ ተናግረዋል። በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ኢንዱስትሪ ባለሙያ አቶ አቢቹ ሀይለማርያም በበኩላቸው የክልሉ ቅርሶች ተሰባስበው የሚታዩበት ሙዚየም ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ የተጣለው ከአንድ አመት በፊት መሆኑን ገልፀዋል። ከባህላዊ እሴትነታቸው ባለፈ ለቱሪዝም ልማት  ጭምር ፋይዳ ያላቸው በርካታ የክልሉ መገለጫ የባህል ቅርሶች ቢኖሩም በተገቢው መልኩ ተደራጅተውና ተሰባስበው ጥቅም ላይ የሚውሉበት መንገድ አለመመቻቸቱን ገልጸዋል። በመሆኑም ክልሎች የብሄረሰቦችን ታሪክና ባህል ለማደራጀት፣ ቅርሶችን ለመጠበቅ፣ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማከናወን ይችሉ ዘንድ ለባህል ማዕከላት የተሻለ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ባለሙያው አሳስበዋል። በዚህ ረገድ የኦሮሚያ ባህል ማዕከል በመልካም አብነት ሊጠቀስ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል፣ ቱሪዝምና መገናኛ ብዙሃን ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሽፈራው ገብረስላሴ በበኩላቸው በአገሪቱ የባህል ማዕከላት እንዲስፋፉ የሚደነግግ መመሪያና ደንብ ቢኖርም ተግባራዊ በማድረግ በኩል ክልሎች ድክመት እንዳለባቸው ገልፀዋል። ''ኢኮኖሚ እድገትና ባህል ተደጋግፈው መሄድ አለባቸው'' የሚሉት አቶ ሽፈራው የህብረተሰቡን አኗኗር ሁኔታና ባህል የሚያሳዩ የባህል ማዕከላትን በማስፋፋት ረገድ ክልሎች ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የምክር ቤቱ አባል አቶ ጠይብ አባፎጊ ኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማስፋት በሰጠችው ትኩረት ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ሌሎች ተጠሪ ተቋማት እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ይገልፃሉ። የማይዳሰሱ ቅርሶችና ባህሎችን በሚገባው ልክ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ቀሪ ስራዎች እንዳሉ አመልክተዋል። እነዚህን ባህሎች በማጎልበት ባህልን ጠብቆ ለማቆየትና የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ደግሞ የባህል ማዕከላት አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም