ለከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች የማዕረግ ሹመት ተሰጠ

126
(ኢዜአ) ጥር 9 / 2012  ለከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች የማዕረግ ሹመት የመስጠት ስነ ስርዓት ተከናወነ። በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዣዥ ዶክተር ዐቢይ አህመድ አቅራቢነት በኢፊዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የማዕረግ ሹመቱን ተሰጥተዋል። የማዕረግ ሹመት አሰጣጡ ላይ ንግግር ያደረጉት የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አህመድ “በሀገሩ የሚኮራ፤ ሀገሩን የሚያኮራ፤ ለዘመናት ጀግንነቱን ያስመሰከረ፤ ድል ማድረግ ዜማው ፤ ማሸነፍ ቋንቋው የሆነ፤ የራሱን የማይሰጥ የሰውን የማይወስድ እንዲሁም ሰላምን ከፍ ለማድረግ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ” ብለውታል የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊትን። መከላከያ ሰራዊቱ በውስጥ ሰላምና ደህንነትን በውጪ ድንበርና ሉዓላዊነትን እያስከበረ ይገኛል ብለዋል የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዣዡ። ከድሆች ጓዳ እስከ ገበሬው አጨዳ ተሰማርቶም የሚገኝ ጀግና ሰራዊት መሆኑንም አንስተዋል። ምትክ ለሌላት ሀገራቸው ግንባራቸውን የሚሰጡ ጅግኖችን ሀገሪቱ ማፍራት ቀጥላለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ዛሬም ለሹመት የበቁት ወታደራዊ አመራሮች ለዚህ አብነት መሆናቸውን አንስተዋል። በዛሬው ወታዳራዊ ሹመት አሰጣጥ የሴቶችን እኩልነት ለማሳደግ ቁጥራቸው ከፍ ያሉ ሴት ወታደራዊ አመራሮች ሹመት እንደተሰጣቸውም ተናግርዋል። ወታዳራዊ ሹመቱም ተዋፅዕዎን የጠበቀ መሆኑንም ገልፀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው መከላከያ ሰራዊቱ የሚቆመው ለህገ መንግስቱ መርሆች መከበር ብቻ መሆኑን በማንሳት ሁሉንም በእኩልነት ነፃ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል። ሰራዊቱ የብሄረሰብም የሃሳብም ብዝሃነት እንዳለ አውቆ ከፓለቲካ ገለልተኛ ሆኖ መቆም የሚችል መሆን አለበትም ነው ያሉት። ማንኛውም ነገር ከሀገር ሉዓላዊነት አይበልጥም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የፓለቲካ ሀይሎች ህገ መንግስቱን አክብረው መንቀሳቀስ ግዴታቸው መሆኑን አስታውቀዋል። ጀነራል መኮንኖች በውሏቸውና በስራቸው እንደሚመዘኑ በማንሳትም ውሏቸውና ስራቸውን እንዲያሳምሩ አሳስበዋል። የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ሁልጊዜ ውግንናው ለህዝብ በመሆኑ በተሰማራባቸው ግዳጆች ሁሉ ውጤታማ ሆኖ መዝለቁንም ገልፀዋል። የዛሬው ሹመት የተሰጣቸው ወታደራዊ መኮንኖች በነበራቸው ሃላፊነት፣ ባስመዘገቡት አፈፃፀም እና በቀጣይም የላቀ ውጤት ያስመዘግባሉ በሚል እምነት መሆኑንም ነው የተናገሩት። በዚህም በአጠቃላይ ለ65 ጄኔራል መኮንኖች የማዕረግ ሹመቱ የተሰጠ ሲሆን ስድስቱ የሌትናል ጀነራል፣ 19 ሜጀር ጀነራልና 40ዎቹ ደግሞ የብርጋዴር ጀነራልነት ማዕረግ የተሰጣቸው መሆኑን የዘገበው ፋና ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም