የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ የብሩንዲ አቻውን 5 ለ 0 አሸነፈ

70
አዲስ አበባ፤ ጥር 9 / 2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የብሩንዲ አቻውን 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸነፈ። በነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም ፓናማ እና ኮስታሪካ በጋራ በሚያዘጋጁት 10ኛው የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ይካሄዳል። በዓለም ዋንጫው ለመሳተፍ የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ በኢንትዋሪ ስታዲየም ያደረገው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የብሩንዲ አቻውን 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ረቷል። ምርቃት ፈለቀ፣ታሪኳ ዴቢሶ፣አረጋሽ ካልሳ፣ረድኤት አስረሳኸኝ እና የብሩንዲዋ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ኬዛ አንጄሊክ በራሷ ግብ ላይ ባስቆጠረችው ግብ ነው ብሔራዊ ቡድኑ ያሸነፈው። በአሰልጣኝ ፍሬው ሃይለገብርኤል የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ያስመዘገበው ውጤት አንድ እግሩን ወደ ቀጣዩ ዙር ያስገባበት ነው ማለት ይቻላል። ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች የመልስ ጨዋታቸውን ከሁለት ሳምንት በኋላ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ያደርጋሉ። በነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም ፓናማ እና ኮስታሪካ በጋራ በሚያዘጋጁት 10ኛው የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ 16 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ። አፍሪካ በዓለም ዋንጫው ሁለት ብሔራዊ ቡድኖችን የማሳተፍ ኮታ አላት። በሌላ የእግር ኳስ ዜና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ተካሄደዋል። በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በእንዳለ ደባልቄና በሀብታሙ ታደሰ ግቦች ሲዳማ ቡናን 2 ለ 1 አሸንፏል። ዳዊት ተፈራ ሲዳማ ቡናን ከሽንፈት ያልታደገችውን ግብ አስቆጥሯል። በክልል ከተሞች ደግሞ ሌሎች ስድስት ጨዋታዎች ተደርገዋል። በትግራይ ስታዲየም የሊጉ መሪ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በናይጄሪያዊ አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ሁለት ግቦች ሰበታ ከተማን 2 ለ 1 አሽንፏል። እንዳለ ዘውገ ለሰበታ ከተማ ብቸኛዋን ግብ አስቆጥሯል። በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባህርዳር ከተማ ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲን 3 ለ 2፣ በሀዋሳ ስታዲየም ሀዋሳ ከተማ ወልቂጤ ከተማን 3 ለ 1፣ በድሬዳዋ ስታዲየም ድሬዳዋ ከተማ አዳማ ከተማን 2 ለ 1 እና በጅማ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ጅማ አባ ጅፋርን 2 ለ 1 አሸንፈዋል። በሆሳዕና ስታዲየም ሀዲያ ሆሳዕና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያካሄዱት ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል። ትናንት በትግራይ ስታዲየም በተደረገው የፕሪሚየር ሊጉ የዘጠነኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ስሑል ሽረ ፋሲል ከነማን 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ19 ነጥብ ሲመራ፣ ፋሲል ከነማና ስሑል ሽረ በተመሳሳይ 15 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። አዳማ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ ከተማ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም