በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስርዓት ለማስፈን እየሰራሁ ነው ... የሳይንስና ከፍተኛ ት/ት ሚኒስቴር

69
አዳማ (ኢዜአ) ጥር  09/2012 የሀገሪቷን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደት ለማረጋገጥና በዘርፉ የሚከናወኑ የለውጥ ሥራዎችን ከዳር ለማድረስ እየሰራ እንደሚገኝ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችል  የቀጣይ 10 ዓመት ረቂቅ የልማት እቅድና ፍኖተ ካርታ ላይ በአዳማ ከተማ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የዘርፉ አመራሮች ጋር የሁለት ቀናት የምክክር መድረክ አካሔዷል ። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንደገለጹት  በዘርፉ የሚከናወኑ የለውጥ ሥራዎችን ከዳር ለማድረስ  ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደቱን ከማረጋገጥ ባለፈ የሀገሪቷን የከፍትኛ ትምህርት ተቋማት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችሉ እቅዶች ተዘጋጅተዋል ብለዋል። የዘርፉን ረቅቅ እቅድ የሀገሪቷን የትምህርትና ስልጠና ሂደት ከመሰረቱ የሚቀይር ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ በተለይም ለትምህርት ጥራትናለሳይንስና ቴክኖሎጂ ልዩ ትኩረት የሰጠ ነው ብለዋል ። ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮ፣በልህቀት፣በጥናትና ምርምር ሥራዎች ማደራጀት ሌላኛው የእቅዱ ቀዳሚ ተግባር መሆኑንም ጨምረው ገልጠዋል። የመድረኩ ዓላማ ረቅቅ የልማት እቅዱን ወደ ተግባር ለማስገባት ከትምህርት ማህበረሰብ ፣ከባለደርሻ አካላትና ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ግብዓት ለማሰባሰብና ለማዳበር ነው ብለዋል። በእስከ አሁኑ ሂደት የነበረው የሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥርዓተ ትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተገለበጠ በመሆኑ ይህን ከመሰረቱ ለመቀየርና የተቋማቱ ተልዕኮ ከሀገሪቷ የወቅቱ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፍላጎት ጋር የተቆራኘ ለማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል። በ50 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችና በሁሉም የቴክኒክናሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች ተግባራዊ የሚሆን ረቂቅ የልማት እቅድ መሆኑን የገለጹት ሚኒስቴር ዴኤታው የመንግስትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከዚህ አንፃር የተቃኙ ይሆናሉ ብለዋል። ጥራት ያለው የሰው ሃይል ለማፍራት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ወጥነት ባለው ሥርዓተ ትምህርት ብቻ እንዲመሩና መካክለኛ ሙሁራን በተመሳሳይ ደረጃ ለማፍራት ጭምር ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል ። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እሚዬ ቢተው  በበኩላቸው በተያዘው የበጀት ዓመት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዘርፉ መሰረታዊ ሪፎርም ለማምጣትና ሰላማዊ የመማር መስተማር ሂደት ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ገልጠዋል። የልማቱ የመነሻ እቅድ እንደ ሀገር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ የሚወስድ ነው ያሉት ሰብሳቢዋ ብቁ ትውልድን በአመለካከት፣ክህሎትና በእውቀት በማፍራት ዘርፉን  የሚያሻግር መሆኑንም በግምገማው ተመልክተናል ነው ያሉት። ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ያዘጋጀውን ረቅቅ የልማት እቅድ የማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች ፣ስልቶችና ማኑዋሎችን ወደ ህዝብ በማውረድ ሁሉም የትምህርት ማህብረሰብ በማሳተፍና በቂ ግብዓት በማከተት ወደ ተግባር እንዲገባ አቅጣጫ መስጠቱንም አመልክተዋል። በሌላ በኩል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲረገጋጥ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ እስከ ልማት እቅዱ ዝግጅት ድረስ ያደረገው ጥረት አበረታች መሆኑን ተናግረዋል። በእንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች በተፈጠረው የፀጥታ ችግር መደበኛ ትምህርት አቋርጠው ወደ ቤተሰቦቻቸው የተመለሱ ከ35 ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ቀጣይ ቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባል  ብለዋል ። በተቋማቱ የተስተዋሉት ችግሮች ውጫዊ የፖለቲካ አጀንዳ ናቸው ያሉት ሰብሳቢዋ ይህን ማነቆ ለማለፍና በዘላቂነት የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አስገዝበዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም