አንድ ግለሰብ በ12 ሚልዮን ብር ያስገነቡትን ጤና ጣብያ ለማህበረሰቡ አስረከቡ

157

ሽረ እንዳስላሰ (ኢዜአ) ጥር 9 / 2012 በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ በአንድ በጎ አድራጊ ግለሰብ በ12 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ አንድ ጤና ጣቢያ ዛሬ ተመረቆ ለህብረተሰቡ ተላለፈ ። በአሜሪካን አገር የሚኖሩ ወይዘሮ ሄለን ወረደ በተባሉ በጎ አድራጊ ግለሰብ የተገነባው ጤና ጣቢያ የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሓጎስ ጎደፋይ በተገኙበት ዛሬ ተመርቋል ።

ጤና ጣቢያው ለከተማዋ ነዋሪ ህዝብና በቅርብ ርቀት ለሚገኙ የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች በቀላሉ የሚገለገሉበት መሆኑን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ዝናቡ ደስታ ገልፀዋል ።

ደረጃውን የጠበቀ ጤና ጣቢያ ሰርተው ለአካባቢው ህብረተሰብ ያስረከቡት በጎ አድራጊዋ ወይዘሮ ሄለን ወረደ በበኩላቸው ለወደፊቱ ጤና ጣቢያው ወደ ሆስፒታል ለማሳደግ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል ።

ጤና ጣቢያው በአሜሪካ ከሶስት አመት በፊት በእሳት አደጋ ምክንያት ህይወታቸው ያጡ  አምስት ልጆቻቸው ስም “ ፋይፍ ኢንጅልስ ጤና ጣቢያ” ተብሎ እንዲሰየም መደረጉ ደስታ እንደፈጠረላቸውም ወይዘሮዋ ተናግረዋል ።

ጤና ጣቢያው ከሃያ አምስት ሺህ ለሚበልጥ ህዝብ የጤና አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳለው የተናገሩት ደግሞ የከተማዋ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ ወይዘሪት ኢትዮጵያ ሲሳይ ናቸው።

 ጤና ጣቢያው ለተለያዩ የህክምና አገልግሎቶች የሚውሉ አስራ ስድት ክፍሎች ያካተተና ምቹ የታካሚዎች ማረፍያ ክፍሎች ያሟላ ነው ተብሏል ።

የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሓጎስ ጎደፋይ ጤና ጣቢያው በመረቁበት ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማረጋገጥ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ የበጎ አድራጊ ግለሰቦች እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነው ብለዋል ።

የዚሁ አንድ አካል የሆነውና  በወይዘሮሮ ሄለን ወረደ የተገነባው ጤና ጣቢያም የጤና አገልግሎቱ ተደራሽነት ለማጠናከር  ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል ።

የክልሉ ጤና ቢሮም አስፈላጊውን የጤና ባለሙያዎችና የህክምና ቁሳቁስ በፍጥነት በማሟላት በአጭር ጊዜ ውስጥ  ለአገልግሎት እንዲበቃ ይደረጋል ብለዋል ።

በሌላ በኩል በሽረ እንዳስላሴ ከተማ አሥር ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ለመገንባት ለተያዘው እቅድ እገዛ የሚውል የከተማዋ ነጋዴዎችና ባለ ሃብቶች ከአስር ሚሊዮን ብር በላይ ለግሰዋል ።

በከተማዋ ነዋሪ ህዝብና በመንግስት ትብብር ከ320 ሚሊዮን ብር በሚበል ወጪ አሥር ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ ነው።

ለዚሁ ዓላማ እንዲውል ትናንት በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ አሥር ሚሊዮን ብር ድጋፍ መገኘቱን የአስፋልት መንገዱ  አሰሪ ኮሜቴ ሰብሳቢ ኮሎኔል ደሳለኝ ገብረስላሴ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም