አገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻያው ዘላቂ ዕድገትን ታሳቢ ሊያደርግ ይገባል

44
አዲስ አበባ   (ኢዜአ) ጥር 09/2012  አገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻያው በአገር ውስጥ ሃብት ላይ የተመሰረተ ዘላቂ የምጣኔ ሃብት ዕድገትን ታሳቢ እንዲያደርግ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው  ዶክተር ጉቱ ቴሶ ጠቆሙ። እኚህ የምጣኔ ሃብት ተንታኝ ለኢዜአ ሲናገሩ ኢትዮጵያ ባለፉት 15 ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ስታስመዘግብ መቆየቷን አስታውሰዋል። ይሁንና ዕድገቱ በአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ያልተመሰረተና ከሌሎች አገራት የተቀዳ በመሆኑ አንድ ቦታ ላይ ቆሟል የሚል ሙያዊ አስተያየት አላቸው። እንደ ቻይናና ኮሪያ ያሉ አገራት የምጣኔ ሃብት ዕድገታቸው የራሳቸው ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ መሰረትና መገለጫ እንዳለው ያስረዳሉ። በመሆኑም ኢትዮጵያ ካለፈው ትምህርት በመውሰድ በአገር ውስጥ ሃብት ላይ የተመሰረተ የአገር በቀል ምጣኔ ሃብት ዕድገት ስትራቴጂ እንደሚያስፈልጋት ነው በአፅንኦት ያነሱት። እንደ ባለሙያው ገለጻ የሚቀረፁ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ስትራቴጂዎች አገሪቷ በረዥም ጊዜ ለመድረስ የያዘችውን ዕቅድ ታሳቢ ሊያደርጉ ይገባል። በማሻሻያው ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የተካሄዱ ውይይቶችን ጠቀሜታ በመግለጽም በቀጣይ ከከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ተቋማት፣ ከሙያ ማዕከላትና ከሌሎችም ጋር ተመሳሳይ ውይይቶችን በማድረግ መንግስት ግብዓት መሰብሰብ እንዳለበት መክረዋል። የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ጉቱ አካታች ለሆነ ዕድገት በተለያየ መንገድ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል። የገንዘብ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ በበኩላቸው ከምጣኔ ሃብት ማሻሻያው ጎን ለጎን ካለፉት ዓመታት የተሻለ ተሞክሮ ያላቸውን ልምዶች በመውሰድ ወደ ተግባር ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። መንግስት ወደ ብልፅግና ለመሸጋገር አገር በቀል የምጣኔ ሃብት ዕድገት ስትራቴጂ ለመተግበር እየሰራ እንደሆነም አክለዋል። አዲሱ ማሻሻያ ሲተገበር የአገር ውስጥ ሃብትን ጥቅም ላይ በማዋል ተቀዛቅዞ የነበረው የምጣኔ ሃብት ዕድገት ያንሰራራል ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ዜጎቿን በተለያየ መንገድ ከድህነት ለማውጣት በአገር በቀል እውቀት ላይ የተመሰረተ አገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ ስትራቴጂ እያዘጋጀች ትገኛለች። የገንዘብ ተቋማትን ማሻሻል፣ ታክስ /ገቢ/ የመሰብሰብ አቅምን ማሳደግ፣ የማዕድን ልማትና ሌሎችም በአገር በቀል ማሻሻያው ተካተዋል። የምጣኔ ሃብት ማሻሻያውን ተግባራዊ ለማድረግም የዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ.ኤም.ኤፍ በብድርና በድጋፍ መልክ ስድስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማፅደቃቸው ይታወሳል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም