በጎንደር የጥምቀት በዓል ላይ ፍንዳታ ለመፈፀም በዝግጅት ላይ የነበሩ የጥፋት ቡድኖች በቁጥጥር ስር ዋሉ

51

አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2012 በጎንደር በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ በተኩስ የተቀናጀ ከፍተኛ ፍንዳታ ለመፈፀም በዝግጅት ላይ የነበሩ ሁለት የጥፋት ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በላከው መግለጫ እንደገለጸው በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ ዘንድሮ በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ በተኩስ የተቀናጀ ከፍተኛ ፍንዳታ ለመፈፀም የሽብር ተልዕኮ ተቀብለው በዝግጅት ላይ የነበሩ ሁለት የጥፋት ቡድን አባላት ከአራት ኤፍ ዋን ቦምብ እና ከ200 ጥይቶች ጋር በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ክትትል እንዲሁም በሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ በአማራ ክልል ፀጥታ ሀይሎች እና በአካባቢው ህብረተሰብ ትብብር በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የጥፋት ቡድን ያሰማራውን አካል በቀጣይ ይፋ እንደሚያደርግም ገልጾ፤የጥፋት ሀይሎቹ አደጋውን ቢያደርሱ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እና መኖሪያ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚሰጣቸው ቃል የተገባላቸው መሆኑንም አረጋግጧ።

የፀጥታ ሀይሎች በቁርጠኝነት መስራታቸውና የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በመጠበቃቸው በዘንድሮው የጎንደር የጥምቀት በዓል ታዳሚዎች ላይ ሽብር በመፈፀም የንፁሃን ዜገችን ህይወት ለመቅጠፍና በንብረት ላይ አደጋ ለማድረስ የታለመውን አደጋ ማክሸፍ መቻሉም ተገልጿል፡፡

ዘንድሮ በመላው ሀገሪቱ በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ተመሳሳይ ተልዕኮ ያላቸው አካላት እኩይ ተግባራቸውን ሊፈፅሙ ስሚችሉ ህብረተሰቡ በአካባቢው ከሚገኘው የፀጥታ ሀይል ጋር በመቀናጀት ሰላሙን እንዲጠብቅም ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም