የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ የአብሮነት እሴቶች መገለጫ መሆኑ ተገለጸ

112
ጥር 08/2012 (ኢዜአ)  የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ የአብሮነት እሴቶቻችን መገለጫ በመሆኑ በዩኔስኮ መመዝገቡ የሃገር ሃብትነቱን ከፍ እንደሚያደርገው በትግራይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች ገለጹ። አል ነጃሺና መስጂድና ሌሎች ታሪካዊ የእስልምና ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። የትግራይ ማዕከላዊ ዞን የእልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሊቀ መንበር ሺህ መህመድ ስዒድ ውሃብ እንደገለጹት ሀገራችን ገና ያልተዳሰሱ እና የአለም ማህበረሰብ ሊያውቃቸው የሚገቡ ቅርሶች አሏት። እነሱን በአለም ቅርስነት በማስመዝገብ የቱሪስት ፍሰት እንዲጨመር አበረታች ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው በሙስሊም ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ታሪካዊ መስጊዶች እና የመሸአክ ስፍራዎችም ለቱሪዝም ልማት እንዲውሉ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። “በተለይ የአልነጃሽ ታሪካዊ ስፍራን በአለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ሊሰራበት ይገባል” ብለዋል። በአክሱም ከተማ የሐየሎም ቀበሌ ነዋሪ አቶ መስጠፋ ዓሊ በበኩላቸው “የጥምቀት በዓል በአለም ቅርስነት መመዝገቡ የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮችም ደስታ ነው” ብለዋል። “ለሀገር ኢኮኖሚ እና ገጽታ ግንባታም ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ብለዋል። “በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሙስሊም ሃይማኖት በመቀበል እምነታቸውንና ሀይማኖታቸውን በነጻነት እንዲያስፋፉ የተደረገበትን የአልነጃሽ ስፍራ በአለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረቱ ሊቀጥል ይገባል” ብለዋል። በችግርና በደስታ ጊዜ ሙስሊም ክርስቲያኑ በአድነትና በመተባበር እንደሚያሳልፉት የገለጹት ደግሞ የውቅሮ ማራይ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ጀሚላ ሀሰን “የጥምቀት በዓል በአለም ቅርስነት መመዝገቡ ደስታው ሁላችንንም ይመለከታል”ሲሉ ገልጸውታል ። የጥምቀት በዓል የእምነታችን ፣ የባህላችን እሴቶቻችን ብዝህነት አንዱ መገለጫ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮዋ “አብሮነታችንን ማበለጸግ እና ለአለም ማስተዋወቅ ይገባል” ብለዋል። “ኢትዮጵያዊያን የተለያየ ሃይማኖት፣ባህልና ቋንቋ ቢኖረንም ልዩነታችን ውበታችን በመሆኑ በአንድነት እና በፍቅር ሀገራችንን ማልማት ይገባናል” ብለዋል። አክሱም የሚገኘው የሳቢያን አለም አቀፍ ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው አብርሃ እንዳሉት የጥምቀት በዓልን ለመታደም ለሚመጡ እንግዶች የቆይታ ጊዜአቸውን እንዲያራዝሙ ጥሩ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። ሆቴልና ቱሪዝም የማይነጣጠሉ እና ተመጋገበው የሚሄዱ መሆናቸውን ገልጸው በበዓሉ ምክንያት ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ አለመኖሩንም ጠቁመዋል። በዓሉን ለማክበር ለሚመጡ የውጭ ቱሪስቶች ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ 44 የመኝታ ክፍሎች እንደተያዘ እና ካለፈው አመት  ብዛት እንዳለው አቶ ጌታቸው ተናግረዋል። የአርማህ አለም አቀፍ ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ ፍርዲ መኮንን በበኩላቸው እንደተናገሩት የሆቴልና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለሰላም እና ለቱሪዝም እድገት በጋራ ሊሰሩ የሚገባ በመሆኑ እነሱም ትኩረት አድርገውበታል። የቱሪዝም ዘርፍ የስራ እድል መፍጠር ለሀገር ገጽታ የማይተካ ሚና አለው ያሉት ስራ አስኪያጁ ከሳምንት በፊት ሁሉም ማረፊያ ክፍሎቻቸው በውጭ እንግዶች መያዛቸውን ተናግረዋል
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም