የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ሰላምን ለማስፈን እንሰራለን - የአጎራባች ዞኖች አመራሮች

93
ጋምቤላ ጥር 8 ቀን 2012 (ኢዜአ)   የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በጋራ እንደሚሰሩ የጋምቤላ፣ የደቡብና የኦሮሚያ ክልል አጎራባች ዞኖች ገለጹ፡፡ ዞኖቹ  ለጋራ ሰላም እንደሚሰሩ የገለጹት በጋምቤላ ክልል በማጃንግ ዞን ያለውን ሰላም በማስመልከት በህብረተሰቡ በተዘጋጀው የምስጋና ስርዓት ላይ ነው፡፡ የዞን ኃላፊዎቹ ለኢዜአ እንደገለጹት በህብረተሰቡ ዘንድ የቆየውን ግንኙነት በማጠናከርና ለአካባቢው ሰላም ችግር የሚፈጥሩ አካላትን በጋራ በመታገል ለጋራ ልማት ይሰራሉ። በደቡብ ክልል የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዘነ ዳሾ እንዳሉት በማጃንግ ዞን ያለው ሰላምና የህብረተሰቡ አንድነት፣መቻቻልና መተሳሰብ ለሌሎችም አካባቢዎች ትምህርት የሚሆን ነው። "የአገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የወጣት አደረጃጀቶችና በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ለአካባቢው ሰላም መስፈን የሚያደርጉት ጥረት የሚደነቅ ነው" ብለዋል። ተሞክሮውን በዞናቸው ተግባራዊ ለማድረግ ድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል። በዞኑ የተለያየ እምነት ተከታዮችና ቋንቋ ተናጋሪዎች በአንድነትና በአብሮነት ተከባብረውና ተቻችለው በአንድነት መኖራቸው ለአካባቢው ሰላም አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል። "የኅብረተሰቡ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በጋራ እንሰራለን " ብለዋል። በሸካ ዞን ያለውን የጸጥታ ችግር ሙሉ ለሙሉ በመፍታት የአካባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ ህዝባዊ ኮንፈረንሶችን ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፣ ከማጃንግና ከቤንች ሼኮ ዞኖች ጋር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የኢሉአባቡር ዞን ተወካይ አቶ ሰለሞን ታምሩ በበኩላቸው በማጃንግ ዞን ያለውን ሰላምና የህዝብ አንድነት ወደ ዞናቸው በመውሰድ ሰላምን  እንዲኖር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ በዞኖቹ መካከል ያለውን የተጠናከረ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማስቀጠልና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። እንደ አገር የተጀመረው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የብልጽግና ጉዞውን ስኬታማ ለማድረግ ዞኖቹ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ "የማጃንግ ዞን ከነበረበት የሰላም ችግር ወጥቶ ባለፉት ዓመታት ያሳየው የተረጋጋና ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለቴፒ ከተማና አካባቢው ኅብረተሰብና አስተዳደርትምህርት የሚሰጥ ነው" ያሉት ደግሞ የቴፒ ከተማ ከንቲባ አቶ ጢሞቲዮስ ሙሉጌታ ናቸው። "ተሞክሮውን በመውሰድ የከተማውን ሰላም ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል " ብለዋል። አመራሩና ኅብረተሰቡ ለአካባቢው ሰላም መጠበቅ በጋራ የሚሰሩበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በጋምቤላ ክልል የኢታንግ ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኦኬሎ ኡባንግ ልዩ ወረዳው በተደጋጋሚ የሰላም ችግር እንደሚገጥመው ተናግረዋል ። ከማጃንግ ዞን የተገኘው ተሞክሮ በልዩ ወረዳው የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመከላከልና መቆጣጠር ያስችላል ብለዋል፡፡ የሰላምና የአንድነት መድረኮችን በመፍጠርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን አጠናክሮ በማስቀጠል የወረዳው ህዝብ የተሻለ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ የሚሆንበት እድል ለመፍጠር እንደሚሰራ አመላክተዋል። የማጃንግ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሴ ጋጀት በዞኑ ያለውን ሰላምና የኅብረተሰቡን አንድነት አጠናክሮ ከማስቀጠል ጎን ለጎን ልማት ላይ በማተኮር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ "ለዚህም ስኬታማነት በአመራሩና በኅብረተሰቡ ያለው ግንኙነት መጠናከር አለበት" ብለዋል፡፡ የአካባቢውን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥና ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣት ዞኖቹ በቀጣይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሰሩ አስተዳዳሪዎቹ አስታውቀዋል። በማጃንግ ዞን ያለውን ሰላምና አንድነት በማስመልከት በተዘጋጀው ስነ ስርዓት ላይ ከጋምቤላ፣ ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልሎችና ከአጎራባች ዞኖች የተውጣጡ አመራሮች፣ የህዝብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም