ለእርቀ ሰላም ኮሚሽኑ ስኬታማ ስራ አስፍላጊውን እገዛ እናደርጋለን…አቶ ኦርዲን በድሪ

61
ሀረር ጥር 08/2012 (ኢዜአ) በአገሪቱ ዘለቂ ሰላም እንዲሰፍን የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ለሚያደርገው እንቅሰቃሴ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ። የኮምሽኑ አባላት በዛሬው እለት ከሀረሪ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ከክልሉ ካቢኔ አባላት ከሌሎች የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት መንግስት በአገሪቱ የጸጥታ መደፍረስ ችግሮች በእርቅ ተፈተው ዘላቂ ሰላም እንዲኖር በማሰብ ኮምሽኑን ማቋቋሙ ወቅቱን የጠበቀና ተገቢነት ያለው ነው። “ኮሚሽኑ የተጀመረው ሀገራዊ የለውጥ እንቅሰቃሴ ቀጣይነት እንዲኖረው ከማድረግ አንጻር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። “የክልሉ መንግስትም አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ያረጋገጡት ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይም በክልሉ ለዘመናት የቆየው የሰላም ፣የመከባበርና የመቻቻል እንዲሁም የአብሮነት አሴትን ለማስፋት በጋራ እንሰራለን”  ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም የክልሉ መንግስት በባለቤትነት መስራት የሚገባውን ስራዎች እንደሚያከናውን ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል። የኮምሽኑ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ በበኩላቸው እንደገለጹት ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ እራሱን ከማደራጀት ጀምሮ በአገሪቱ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል ። “የኮሚሽኑ ዋና ዓላማ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ መስራት ነው” ያሉት ምክትል ኮምሽነሯ “ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ሲሉ” ተናግረዋል። “ከጥንት ጀምሮ በህዝብ መካከል ችግር የለም ችግሩ የስልጣን ነው ስለሆነም ይህንን ለትውልዱ ማስተማር ይገባል ያሉት ደግሞ የኮምሽኑ አባል የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካርያ ናቸው። “በክልሉ በርካታ እሴቶች ይገኛሉ፤በተለይም አብሮ የመኖርና የመተሳሰብ እሴትን በማጠናከርና ተሞክሮውን ማስፋት ይገባል” ብለዋል። በውይይቱ የተገኙ የክልሉ የካቢኔ አባላት እና አመራሮች በበኩላቸው የኮሚሽኑ መቋቋም አስፈላጊና የሚከሰቱ ችግሮች በእርቅ ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው ስራዎቹን በተጠናከረ መልኩ ማከናወን እንደሚገባም ጠቁመዋል። በውይይቱ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር ኢድሪስ እና አባ ገዳ ጎበና ሆላ እና ሌሎች የኮምሽኑ አባላት ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም