ተጨማሪ ታሪካዊ ቅርሶችን በጥናት በመለየት ለቱሪስቶች እያስተዋወቀ መሆኑን የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ገለጸ

58

ጥር 8/2012 (ኢዜአ) የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን በማስተዋወቅ እና በማልማት የቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን አስታወቀ።

በዩኒቨርሲቲው በአርኪዮሎጂና ሆቴል ኢንስቲዩቲት የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ሓድጉ ዘርኡ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ዩኒቨርስቲው የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችና ጥንታዊ ቅርሶችን በማልማት እና በማስተዋወቅ ላይ ነው።

“የአከባቢው የቱሪዝም ልማት እንዲያድግና የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም ሰፊ ስራ እያከናወነ ነው” ያሉት አቶ ሓድጉ፣ “መስህብ ስፍራዎቹን የሚያመላክት መጽሐፍ በ250 ሺህ ብር ወጪ አሳትሟል” ብለዋል።

“የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስተያየት ሰጥተውበት ለህትመት የበቃው መጽሃፉ በትግራይ ክልል ያሉትን እምቅ የቱሪዝም ሃብቶችን በማስተዋወቅ የቱሪዘም ኢንዱስትሪውን እንዲያሳድግ ተስፋ ተጥሎበታል” ብለዋል።

“በቁፋሮ የተገኙ የተለያዩ የንግድ፣የእርሻ ጥንታዊ መሳሪያ እና የእደ-ጥበብ ውጤቶችም ሙዚየም ውስጥ እንዲጠበቁ ተደርጓል” ያሉት አስተባባሪው፣”በትግራይ ማእከላዊና ሰሜናዊ ምዕራብ ዞኖች በጥናት የተለዩ 22 የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች በዩኒቨርሲቲው ምርምርና ጥናት የተገኙ ውጤቶች ናቸው” ብለዋል።

እምቅ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎቹ የተገኙት በዞኖቹ በጧንቋ አበርገለ፣በመረብ ለኸ፣ዓድዋ፣ ታሕታይ እና ላዕላይ ማይጨው፣መደባይ ዛና እና ታሕታይ ቆራሮ ወረዳዎች ውስጥ መሆኑን አቶ ሐድጉ ተናግረዋል።

''በይሓ፣ማይ አድራሻ እና ቤት ሰማእቲ'' በተባሉ አከባቢዎች በተደረጉ ተጨማሪ የቁፋሮ ስራዎችም የጀርመን፣ጣሊያን እና የአሜሪካ ተመራማሪዎች ከዩኒቨርስቲው ጋር በመተባበር እየሰሩ ሲሆን፣በዘርፉ የዩኒቨርሲቲው ምሁራንና ተማሪዎች የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እያገኙበት ነው” ብለዋል።

ዪኒቨርስቲው በሆቴልና አገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ለተሰማሩ ተቋማት ተከታታይ ስልጠና በመስጠት ሀገራዊ ሃላፊነቱ እየተወጣ መሆኑንም አስተባባሪው ተናግረዋል።

ከቱሪዝም ዘርፍ ሊገኝ የሚችለውን ገቢና ጥቅም ለማሳደግ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ስራ በማከናወኑ የገቦ ዱራ፣ሰግላሜን፣ዓዲ ፀሓፊት እና ሌሎች ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ጥንታዊ ቅርሶችን ለመስህብነት እንዲመረጡ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ቅርሶቹ ከፍተኛ የትምህርት፣የማንነት፣የስልጣኔ ማሳያና የምርምር ጠቀሜታ ስላላቸዉ መንግስት ፣ ህብረተሰቡ፣የምርምር ተቋማት፣አስጎብኚዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ ቅርሶቹን የመታደግ ስራ ሊያከናዉኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአክሱምና አከባቢው የቱሪስት መዳረሻ ስፈራዎችን በማጥናት ቅርሶች እንዲታወቁና እንዲጠበቁ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው የማይተካ እገዛ እያደረገ ነው ያሉት ደግሞ በአክሱም ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የአርኪዮሎጂ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አላይ ወልደስላሴ ናቸው።

በተለያዩ ምክንያቶች በቅርሶች ላይ የሚደርሱ አደጋዎች የት አከባቢና በምን ምክንያት እንደሆነ በመለየት መፍትሔ እንዲሰጠው ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የቱሪዝምና ሆቴል ማናጅመንት የትምህርተ ክፍል የሶስተኛ አመት ተማሪ ቆያቸው ስሜነህ በሰጠው አስተያየት “ዩኒቨርሲቲው ባመቻቸው የአከባቢና ቅርስ እንወቅ ፕሮግራም ከማህረሰቡ ጋር በየሳምንቱ ቅዳሜና እሁድ በዞኑ የሚገኙ ቅርሶችን የመጎብኘት እድል አግኝቻለሁ” ብሏል።

,በባለፈው ህዳር ወር በተጀመረው የቅርሶችን እንወቅ ዘመቻ እስከ አሁን በአክሱም፣ዓድዋ እና ደብረዳሞ አከባቢዎች ያሉ ከ40 በላይ መዳረሻዎችን መጎብኘቱን የተናገረው ተማሪ ቆያቸው፣ጉብኝቱ የቱሪዝም ሃብቶችን በማወቅ ለመጠበቅ ድጋፍ እንዲያደርግ እንዳገዘው ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም