የፈጠራ ሀሳቦች ወደ ተግባር መቀየር የሚችሉበት ማዕከል ተቋቋመ

107
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2010 በወረቀት ደረጃ ባክነው ይቀሩ የነበሩ የፈጠራ ሃሳቦችን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚረዳ ማዕከል መቋቋሙ ተገለፀ። የ'መለስ ዜናዊ ቴክኖሎጂ ምርምር ሽግግርና ኢንኪዩቤሽን ማዕከል' የተሰኘው ማዕከል በጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በስድስት ኮሌጆች ቅርንጫፍ እንዳለውም ተገልጿል። የጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ መለሰ ይመር ለኢዜአ እንደተናገሩት ማዕከሉ ልዩ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎችን ስራ የሚያቀላጥፍ ነው። ማዕከሉ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ሰዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲሰሩና ነባር ቴክኖሎጂን ለመቅዳት እንደሚያግዝ ገልፀው፤ በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ ቴክኖሎጂን ሙሉ በሙሉ ለመቅዳት አልሞ እንደሚሰራም ነው ያብራሩት። ለማዕከሉ ህንፃ ግንባታ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን ለውስጥ አደረጃጀት ደግሞ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንና ከ50 በላይ አንቀሳቃሾችን የመቀበል አቅም እንዳለውም ተናግረዋል። በኮሌጁ የመለስ ዜናዊ ቴክኖሎጂ ምርምር ሽግግርና ኢንኪዩቤሽን ማዕከል ጊዜያዊ ዳይሬክተር ወይዘሮ ዋጋዬ ገብረመድህን በበኩላቸው "ማዕከሉ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ለማድረግ ይረዳል" ብለዋል። ከዚህ በፊት በወረቀት ደረጃ ባክነው ይቀሩ የነበሩ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች ወደ ተግባር ተቀይረው ወደ አንቀሳቃሾች እንዲሸጋገሩ በማድረግ የስራ እድል እንደሚፈጥርና የኀብረተሰቡን ኑሮ ለማቅለል አስተዋፅኦ እንዳለውም ተናግረዋል። ማዕከሉ የቪዲዮና ስማርት ኮንፍረንስ  እንዲሁም የምርምርና የኢንኪዩቤሽን ክፍሎችን ያካተተ መሆኑንም ነው የተናገሩት። የፈጠራ ሃሳብ ያለው ማንኛውም ግለሰብ ወደ ማዕከሉ በመምጣት የድጋፉ ተጠቃሚ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል። ሰልጣኞች በስልጠና ወቅት የተለያዩ የቴክኖሎጂ ሃሳቦች ቢኖራቸውም በገንዘብና በሌሎች እገዛዎች አለመኖር "ሃሳባቸውን ወደ ተግባር መቀየር አይችሉም" ነበር ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አንዱአለም ዘውዴ ናቸው። ማዕከሉ ስራ ሲጀምር ግን ልዩ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ የገንዘብ፣ የሃሳብም ሆነ የማሽን ድጋፍ የሚያገኙበት ይሆናል ብለዋል። ማንኛውም ፈጠራ ያለው ቴክኖሎጂው ተሰርቶ በገበያ ሊውል የሚችል ሃሳብ ያለው ግለሰብ ወደ ማዕከሉ በመምጣት አዋጭነቱ ከተጠና በኋላ እገዛውን እንደሚያገኝም ነው ያብራሩት። በጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ካለው ማዕከል በተጨማሪ በስድስት ኮሌጆች ቅርንጫፍ እንዳለው የገለፁት ምክትል ኃላፊው የማዕከሉም ሆነ የቅርንጫፎቹ ግንባታ ተጠናቆ አደረጃጀቱም መሟላቱን ተናግረዋል። ቅርንጫፎቹም በእንጦጦ፣ ንፋስ ስልክ፣ አቃቂ፣ ምስራቅ እና ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች እንዲሁም የካ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በተያዘው ሳምንት መጨረሻ ሰኔ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. የሚመረቀው ይህ ማዕከል  በመጪው ዓመት የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ሰዎች አወዳድሮ ወደ ስራ ይገባልም ተብሏል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም