የድሬ-ዳዋ ዩኒቨርሲቲን ሰላም ለማስጠበቅ አስፍላጊውን እገዛ እናደርጋለን…የሃገር ሽማግሌዎች

123
ድሬዳዋ ፤ጥር 8/2012 (ኢዜአ) በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የተቋረጠው ትምህርት እንዲጀመርና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲጠናከር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ተናገሩ። ለሟችና ተጎጂ ተማሪዎች ቤተሰቦች ተገቢውን ካሳ በመክፈል ጥር 18 ቀን ትምህርት ለመጀመር የታሰበውን ዕቅድ በጋራ ፍሬያማ ማድረግ እንደሚገባም ሽማግሌዎቹ ገልጸዋል። ትምህርት ለማስጀመርና በዩኒቨርሲቲው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ትናንት በተካሄደው ውይይት ላይ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተማሪዎችን በችግር ጊዜ ተረባርበው ወደ የቤታቸው እንደሸኙት ሁሉ አሁንም ተቀብለው እንደወላጅ ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አዛውንቱ መሐመድ ጣሂር ዩኒቨርሲቲው ከመላው ሀገሪቱ የሚመጡ ተማሪዎች በእውቀት የሚታነጹበት  ተቋም መሆኑን ተናግረው፤ ይህንን በመተላለፍ የራሳቸውን የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የመማር ማስተማር ተግባርን የሚበጠብጡ አካላትን ተቀናጅቶ ለመከላከል ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል። "በዩኒቨርሲቲው ሰላም እንዲሰፍን በተናጠልና በጋራ እንሰራለን" ያሉት ደግሞ አቶ ሃምዛ ድላላ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ዩኒቨርሲቲው ችግር በፈጠሩ ተማሪዎችና የጥበቃ ሰራተኞች ላይ እየወሰደ የሚገኘው እርምጃ ተጠያቂ በሆኑ አመራሮች ላይም ሊደገም ይገባል። "ተማሪዎችን መልሰን ለመቀበል ዝግጁ ነን፤ ከሰላም የሚበልጥ ምንም ነገር ስለለሌ ለመማር ማስተማሩ ሰላማዊነትና ዘላቂነት ተግተን እንሰራለን" ብለዋል። ሐጂ አህመድ ኡመር እንዳሉት የዩኒቨርሲቲውን ቅጥር የሚነካ ሁሉ የኢትዮጵያዊያ ጠላት መሆኑን አስታውቀዋል። "የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲሳካ እኛ ኃላፊነታችንን እንወጣለን፤ ማናጅመንቱ ራሱን በአግባቡ መፈተሸ አለበት" ብለዋል። አዛውንቱ መሐመድ ሙስጠፋ "ተማሪዎችን መልሶ በመቀበል የመማር ማስተማር ሥራውን ለመጀመር የታቀደው ተግባር እንዲሳካ ለሟች ተማሪ ቤተሰቦችና ለተጎጂ ተማሪዎች ተገቢውን ካሳ መክፈል ይገባል" ብለዋል፡፡ ችግሩን የፈጠሩትን ደግሞ ለህግ አቅርቦ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል። ተመሣሣይ ሃሳብን ያንፀባረቁት ወጣት ባህሩዲን አብደላሂ በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ የሚገኙ ወጣቶችም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራው ስኬታማ እንዲሆን በተባበረ መንገድ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጧል። ዩኒቨርሲቲው በዙሪያው ላሉ ወጣቶችና ቤተሰቦች ትምህርት ቤት በመክፈት፣ የትምህርት ዕድል በመስጠትና የሥራ ዕድል በማመቻቸት ወጣቱንና ነዋሪውን የዩኒቨርሲቲው ዋስና ጠበቃ ማድረግ እንዳለበትም ጠቁሟል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡባህ አደም በበኩላቸው "ዩኒቨርሲቲው ያለበትን መሰረታዊ ክፍተቶች ደረጃ በደረጃ ለማቃለል የተቀናጀ ሥራ እየሰራ ይገኛል" ብለዋል። በውይይቱ የተነሱ ክፍተቶችንም ትኩረት ሰጥቶ መፍትሄ ለማምጣት እንደሚሰራ ገልጸው በተፈጠረ ሁከትና ብጥብጥ ለሞቱትና ለተጎዱ ቤተሰቦች ካሳ እንደሚሰጥም ተናግረዋል። በተለይ የጥበቃው ሥራ በአስተማማኝ ደረጃ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል። በውይይቱ ላይ የተሣተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ በየደረጃው የሚገኘው ነዋሪ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች የድሬዳዋን የዘመናት መገለጫ ፍቅርና አቃፊነት ለተማሪዎቹ በመለገስ የመማር ማስተማሩን ሂደት ሰላማዊ ለማድረግ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ "የድሬዳዋ አስተዳደር ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመቀናጀት የመማር ማስተማር ሥራው እንዲሳካም ኃላፊነቱን ይወጣል" ብለዋል። በውይይት መድረኩ ላይ በድሬዳዋና አካባቢዋ የሚገኙ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ ወጣቶችና ሴቶች ተሳትፈዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም