የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በድጋፍ ሰልፉ በቦንብ ፍንዳታ ለተጎዱ ሰዎች የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

72
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከትናንት በስቲያ በነበረው የድጋፍ ሰልፍ በቦንብ ፍንዳታ ለተጎዱ ሰዎች የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ። ከንቲባ ድሪባ ኩማ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከተማ አስተዳደሩ ኮሚቴ በማቋቋም ተጎጂዎቹን በዘላቂነት ለማቋቋም እንደሚሰራም ገልፀዋል። ያለፈው ቅዳሜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና አመራራቸው ላመጡት ለውጥ የተደረገው የድጋፍ ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁና ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ እንኳን ተጎጂዎችን ለመርዳት የተደረገው ርብርብ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል። በቦንብ ፍንዳታው  የሁለት ሰዎች ህይዎት ማለፉንና 156 የሚሆኑት ደግሞ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል። ለጥፋቱ ተጠያቂ የሚሆኑትን መንግስት አጣርቶ ለህዝብ ያሳውቃል፤ ጠንከር ያለ እርምጃም ይወስዳል ብለዋል። ተጎጂዎቹን ለመደገፍ የከተማ አስተዳደሩ 10 ሚሊዮን ብር ማበርከቱንም ተናግረዋል። የተጎጂዎችን ማንነትና የጉዳት መጠን የመለየት ስራም እንደተሰራ ተናግረዋል። ተጎጂዎቹ እንዴት መደገፍ አለባቸው? የሚለው ላይ ውይይት ተደርጎ በዘላቂነት ለማቋቋም እርዳታዎችን የሚያሰባስብ ኮሚቴም ተቋቁሟል ብለዋል። ከተማ አስተዳደሩ ከተጎጂዎች እንደማይርቅ ገልፀው፤ የከተማዋ ነዋሪዎችና መላው ኢትዮጵያውያን የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። በአካል መገኘት ለማይችሉ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉበት የባንክ አካውንት ዛሬ እንደሚከፈትና በመገናኛ ብዙሃን እንደሚገለፅም ጠቁመዋል። በአካል ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ ደግሞ ከተማ አስተዳደሩ ድረስ በመቅረብ ማድረስ ይችላሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም