ምሁራን ምክንያታዊነትን መሰረት ያደረጉ መፍትሄ አምጪ ጉዳዮች ላይ ትኩረት መስጠት ይጠበቅባቸዋል

90
ሆሳዕና ጥር 7/ 2012 ምሁራን ምክንያታዊነትን መሰረት ያደረጉ መፍትሄ አምጪ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የተሻለች አገርን የመፍጠር ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቁ፡፡ የደቡብ ክልል ተወላጅ ምሁራን መድረክ በሆሳዕና ከተማ በመካሄድ ላይ ነዉ፡፡ የደቡብ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት  አቶ ሞገስ ባልቻ መድረኩን ሲከፍቱ እንዳሉት ምሁራን እስካሁን አገሪቱ በሄደችበት ርቀት በምክንያታዊነት ላይ በመመስረት የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነዉ። በወቅቱ ዋልታ ረገጥ ሂደቶችን በማስተናገድ ላይ ለምትገኘው አገር ምሁራን የመፍትሄ ሀሳቦችን ማመንጨትና የሀሳብ ልዕልናን መሰረት ያደረጉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለለውጥ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል። ከባዱ አዋቂነት ነገን ያለመ መሆን እንዳለበት የገለጹት አቶ ሞገስ፣ ዋልታ ረገጥ አካሄዶችን በማረም አገሪቱን ካደጉት አገሮች ተርታ እንድትሰለፍ ማድረግ ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡ በመድረኩ ከወራቤ ዩኒቨርስቲ የተሳተፉት አቶ መሐመድ አማን እንዳሉት ምሁራን ምክያታዊነትን መሰረት በማድረግ ብቁ ዜጋን በመፍጠር አገራዊ ለውጡን ማገዝ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ የእኔነትን ሳይሆን የእኛነትን ለትዉልዱ ማስረፅ ከምሁራን የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም  አመልክተዋል፡፡ ያገኘነዉን እዉቀት ለህብረተሰብ ተጠቃሚነት ተግባር ላይ በማዋል የሚጠበቅብንን ማድረግ አለብን ያሉት ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በመድረኩ የተገኙት ዶክተር ያኒያ ሠይድ መክይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ለመገንባት ከምሁራን የሚጠበቀው ዕውቀታቸው መጥቀም ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ምሁራኑ ምክንያታዊነት ላይ የተመረኮዙ ሥራዎች ላይ በማተኮር ለአገራዊ ዕድገት ድርሻችንን  መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም