ፓርቲዎች ለምርጫ 2012 የወጣው የጊዜ ሰሌዳ ጫና ውስጥ ሊከታቸው እንደሚችል ስጋታቸውን ገለጹ

107
አዲስ  አበባ  ጥር፣7/2012 (ኢዜአ)  ፓርቲዎች ምርጫ 2012 የሚካሄደው በክረምት መሓል መሆኑ፣ የእጩዎች ምዝገባ ቀን ማነስና ሌሎች ችግሮች ጫና ሊያበዛባቸው እንደሚችል ስጋታቸውን ገለጹ። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንትና ምርጫ 2012 የሚካሄድበትን የጊዜ ሰሌዳ አስመልክቶ ዋና ዋና ቀናትና ተግባራትን ለውይይት ማቅረቡ ይታወቃል። በዚሁ መሠረት ስድስተኛው ምርጫ ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሆን ሀሳብ አቅርቧል። ቦርዱ የተረጋገጠ ውጤትን ከነሐሴ 11 እስከ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ለማሳወቅ ሀሳብ ቀርቧል። ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎች ከምንም በላይ ምርጫውን በነሓሴ ለማኬሄድ መታሰቡ የጉዞና የመጓጓዣ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ነው ያመለከቱት። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ "ቦርዱ ምርጫውን ለማካሄድ ቁርጠኛ መሆኑ ጥሩ ነገር ነው" ብለዋል። ነገር ግን አሁን ባወጣው ጊዜያዊ ሰሌዳ ፓርቲዎችን ጫና ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል። ከስጋቱ መካከል በጊዜ ሰሌዳው መሠረት ለእጩዎች ምዝገባ የተሰጠው 14 ቀናት ገደብ ያነሰ ጊዜ መሆኑን ይናገራሉ። አቶ ናትናኤል ቦርዱ ስጋታቸውን ተቀብሎ ዳግም እንደሚመለከት ተስፋቸውን ገልጸው፤ አያይዘውም ቦርዱ የምርጫ ሕጉንም ዳግም መመልከት ቢችል ጥሩ እንደሚሆን አሳስበዋል። ሌላው የኦሮሞ ነጻነት ግምባር (ኦነግ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ ደግሞ "ምርጫው በነሓሴ መካሄዱ ከፍተኛ ጫና ያመጣል" ብለዋል። ወሩ ከባድ የክረምት ጊዜ እንደመሆኑ መጠን የምርጫ ቁሰቁሶችን ለማጓጓዝ እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚዎች ለመንቀሳቀስ የሚቸገሩበት ጊዜ እንደሆነም ተናግረዋል። ይህ ችግር ደግሞ የታሰበውን ያህል ነጻ፣ ፍትሓዊና ገለልተኛ ምርጫን ለማካሄድ የሚያግዙትን "ምቹ ሁኔታዎች ያበላሻል" ሲሉ ስጋታቸውን አሳውቀዋል። አቶ ቀጄላ ጫናውን ትንሽ ለመቀነስ ይረዳ ዘንድ የምርጫው ቀን አሁን ከተያዘው ነሓሴ 10 ወደ ነሓሴ 20 ገፋ ቢደረግ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። ለዚህም ምክንያታቸው ከሞላ ጎደል ከነሓሴ 20 ቀን በኋላ "የክረምቱ ጫና እየቀነሰ ይሄዳል" የሚል ሲሆን፤ ይህም በተወሰነ መልኩ ለእንቅስቃሴ እንደሚያመች ጠቁመዋል። ''ችግሮቹ ማሻሻያ ይደረግባቸዋል ብዬ አምናለሁ'' ያሉት አቶ ቀጄላ፤ በአጠቃላይ ቦርዱ ምርጫውን በዚህ ዓመት ለማካሄድ በመወሰኑ ፓርቲያቸው እንደሚያደንቅ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም