ቅንጅታዊ ሥራ ማነስና የተንዛዛ አሰራር ባለሀብቱ በኢንቨስትመንት ሥራ እንዳይሰማራ እንቅፋት እየሆነ ነው...የዘርፉ አመራሮች

58
ባህር ዳር ሰኔ 18/2010 የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ ማነስና የተንዛዛ አሰራር የአገር ውስጥ ባለሀብቱ በኢንቨስትመንት ሥራ በስፋት እንዳይሰማራ ማነቆ እንደሆነበት የዘርፉ አመራሮች ገለጹ። "ለኢንቨስትመንቱ ውጤታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል" በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ዳር ከተማ የተካሄደው 11ኛው የፌዴራልና የክልል ኢንቨስትመንት አስፈጻሚ አካላት የጋራ የምክክር መድረክ ተጠናቋል። በመድረኩ ላይ የዘርፉ አመራሮች እንደገለጹት ኢንቨስትመንቱን ለማፋጠንና ለማሳለጥ ባንኮች፣ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና መሬት አስተዳደር ሚናቸው የጎላ ቢሆንም ተቀናጅተው ባለመስራታቸው የአገር ውስጥ ባለሀብቱ በአግልግሎት ሰጭ ሥራዎች ላይ ብቻ እንዲወሰን  አድርጎታል። የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩማ ዳባ እንዳሉት የባለድርሻ ተቋማት አገልግሎት አሰጣት ኢንቨስትመንትን ለማፋጠን ከግምት ያስገባ ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም ብቻ መሰረት ያደረገ ነው። እንደ አገር የኢንዱስትሪ ሴክተር አዲስ በመሆኑና የባለሀብቱ ግንዛቤ አነስተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ  ተቋማቱ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት በፍጥነት፣ በመግባባትና በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል። "ባለሀብቱ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የገንዘብ ብድርና የመሬት አቅርቦት ቢያገኝም ግንባታውን አጠቃሎ ወደሥራ ለመግባት የመሰረተ ልማት አለመሟላት ተስፋ እያስቆረጠው ነው" ብለዋል። አቶ ኩማ እንዳሉት ኢንዱስትሪ በባህሪው ውጤታማ ለመሆን ረዥም ጊዜ የሚጠይቅ ቢሆንም ለብድር የእፎይታ ጊዜ ባለመኖሩ ምክንያት ባለሀብቶች ሰግተው ብድር ለመቀበል ፍቃደኛ አይሆኑም። "የአገሪቱን ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ለማሳደግ የግል ባለሀብቱ በቀላሉ ወደ ኢንቨስትመንቱ እንዲገባ ማድረግ ግድ" ይላል ብለዋል። ለዚህም የባንኮች የብድር ስርዓት በልዩ ሁኔታ ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች መመቻቸትና የኤሌክትሪክ አገልግሎትም በተለይ ኢንቨስትመንት ቦታዎች ላይ በልዩ ትኩረት መሟላት አለበት። የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ተወካይና የፕሮሞሽንና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይሄነው ዓለም በበኩላቸው "የአገር ውስጥ ባለሃብቱን አቅም ለማሳደግ ባለድርሻ ተቋማትን የሚያስተሳስር ተቋም ሊኖር" ይገባል ብለዋል። ኢንቨስትመንት በባህሪው በብዙ ተቋማትን የሚነካ በመሆኑ ከተቋማቱ አለመናበብ ጋር ተያይዞ ባለሃብቱ ተስፋ እየቆረጠ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ይልቅ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ መሰማራትን እየመረጡ መሆኑንም ገልጸዋል። እንደ አቶ ይሄነው ገለጻ ይህን ለማስተካከል የአገር ውስጥ ባለሀብቱ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላይ በስፋት እንዲሰማራ ባለድርሻ አካላትን አስተሳስሮ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የሚችል ተቋም መቋቋም ያስፈልጋል። የፌዴራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተካ ገብረኢየሱስ በበኩላቸው የአገር ውስጥ ባለሃብቱ የኢንዱስትሪን ጽንሰ ሃሳብ በአግባቡ ተረድቶ እየሰራ አለመሆኑን ተናግረዋል። በየደረጃው ያለው አስፈጻሚ አካላት የኢንቨስትመንት የህግ ማዕቀፍ ምን እንደሆነ የማስገንዘብ ክፍተት መኖሩንም ጠቁመዋል። ባለድርሻ ተቋማትም የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት በኩል በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው ጠቅሰው፣ ችግሩን ለመፍታት በአንድ ተቋም ላይ የሚጣል አለመሆኑንና የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል። ይህንን ለማድረግ ኮሚሽኑ ለአገር ውስጥ ባለሀብቱ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር መዘጋጀቱን አስረድተው በኮሚሽኑ የሚወጡ የህግ ማዕቀፎችን በማስተግበር በኩል በየደረጃው ያሉ አመራሮች ላይ ያለው ውስንነት መስተካከል እንዳለበት አስረድተዋል። "በመሆኑም አስፈጻሚ አካላት አሰራሮችን መዘርጋት ብቻ ሳይሆን ባለሀብቱን ማስረዳትና ከባለድርሻ አካላት ጋር ማቀራረብ ይኖርባቸዋል" ሲሉም ጠቁመዋል ለሦስት ቀን በተካሄደው አገራዊ የኢንቨስትመንት የምክክር መድረክ ላይ ከክልልና ከፌዴራል የተውጣጡ የዘርፉ አመራሮች መሳተፋቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም