ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ የተገዙ ዘመናዊ የሬዲዮ መገናኛ መሳሪያዎችን አሰራጭቻለሁ– የፌዴራል ፖሊስ

4699

አዲስ አበባ፤ ጥር 7/ 2012  (ኢዜአ ) በኢትዮጵያ የፖሊስ ተግባራትን ማጠናከር ይቻል ዘንድ ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገዙ የዲጂታል መገናኛ መሳሪያዎች በመላው አገሪቱ ለሚገኙ ፖሊስ አባላት መሰራጨቱን የፌዴራል ፖሊስ  ኮሚሽን አስታወቀ።

የሬዲዮ መገናኛው የድምፅና ምስል መረጃዎችን ለማእከል በማቀበል ፈጣንና አስተማማኝ የፖሊስ ተግባር ለማከናወን ያግዛል ተብሏል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በተያዘው በጀት ዓመት ለፈጥኖ ደራሽ መረጃ ክፍሎች በ141 ሚሊዮን ብር የረጅም ርቀት ሬዲዮ መገናኛዎች ግዥ የሚፈጽም መሆኑንም አስታውቋል።

ለፖሊሳዊ ተልዕኮ  የሚያገለግሉት 763 ዘመናዊ ዲጂታል ሞቶሮላ የሬዲዮ መገናኛዎች እስራኤል ከሚገኘው የሞቶሮላ ኩባንያ በ51 ሚሊዮን 884 ሺህ ብር ግዠ መፈጸሙ ታውቋል።

ከእነዚህም ውስጥ 5 መቶዎቹ ለፖሊስ አባላት መሰራጨቱን የፌዴራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ለኢዜአ አረጋግጧል።

ሞቶሮላ የሬዲዮ መገናኛዉን ከሌሎች የሬዲዮ መገናኛዎች ለየት የሚያደርገዉ ማንኛዉም ሰዉ ሲጠቀም የትም ቦታ ላይ ሆኖ ለመቆጣጠር አመቺ በመሆነ ነዉ።

ኔትዎርክ በሚቋረጥበት ጊዜም የግንኙነት ሂደቱ በማይክሮዌቭ የሚደረግ በመሆኑ ረጂም ርቀት ላይ ካሉት አባላት ጋር የመገናኘት እድል ይሰጣል።

ቀደሞ በተቋሙ በነበሩት ሬዲዮ መገናኛዎች ጥሪዎችን ተቀብለዉ ከማስተላለፍ ዉጭ የመረጃ አቀባዩን ማንነት መለየት የማይቻል የነበረ ሲሆን ሞቶሮላ የሬዲዮ መገናኛዉ ግን ምስሎችን ጭምር በመቅረፅ ማዕከል ላለዉ አካል መረጃዎችን ማቀበል እንደሚችል ታውቋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በዚህ ዓመት በ9ኙ ክልሎች ለሚገኙ የፌጥኖ ደራሽ መረጃ ክፍሎች የረጅም ርቀት ሬዲዮ መገናኛዎች ግዥ ለመፈፀም 141 ሚሊየን ብር በጀትመመደቡንም አስታውቋል።

በዚህ መሰረት በሚቀጥሉት አራት ወራት ከተለያዩ አቅራቢዎች ግዥዎችን እንደሚፈጽም ይጠበቃል።