የኤርትራ መንግሥት የልኡካን ቡድን በያዝነው ሳምንት አዲስ አበባ ይገባል

70
አዲስ አበባ ሰኔ 18/2010 የኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በያዝነው ሳምንት አዲስ አበባ ይገባል። የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የሰላም ጥሪ በመቀበል የኤርትራ መንግስት ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ መግለጻቸው ይታወሳል። በዚህም መሰረት የኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በያዝነው ሳምንት አዲስ አበባ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ለዓመታት ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እልባት እንዲያገኝና ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው። በተጨማሪም ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የአልጀርሱን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑም ይታወቃል። ኤርትራ  የሰላም ጥሪውን በመቀበል ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ለመላክ መዘጋጀቷ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ መገለጹን ተከትሎ እርምጃው ሁለቱን አገሮች እንደሚጠቅም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መግለጻቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮችና ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በድንበር ጉዳይ ላይ የሚነሱ ጉዳዮችን በውይይትና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት መንግስት እንደሚሰራ ገልጸው ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም