ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብጽ ሲያካሂዱት የነበረው ውይይት በጥሩ ውጤት ተጠናቀቀ

50

ኢዜአ፤ ጥር 6/2012 የኢትዮጵያ፣ የግብጽ እና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የውሃ ሃብት ሚኒስትሮች እና የልዑካን ቡድኖቻቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እኤአ ከጃንዋሪ 13 እስከ 15 ቀን 2020 በዋሽንግተን ዲሲ ሲያካሂዱት የነበረው ውይይት በጥሩ ውጤት ተጠናቋል።

ውይይቱ የተካሄደው የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስቴቬን ሙንሺን እና የአለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ በተገኙበት ነበር።

ውይይቱ ከዚህ ቀደም ተቋርጦ የነበረውን የቴክኒክ ውይይት በማስቀጠል በሶስቱ አገራት ዋና ከተሞች በአራት ዙር በውሃ ሃብት ሚኒስትሮች ሰብሳቢነት እንዲሁም በዋሽንግተን ዲሲ በሶስት ዙር በተካሄዱት ውይይቶች ዙሪያ ሪፖርት ቀርቦ የስትራቴጂካዊ ውይይት በማድረግ በመግባባት ተጠናቋል።

ከዚህም በመነሳት በእስካሁኖቹ የድርድር ሂደቶች የነበሩትን ልዩነቶች በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ በመፍታት ወደ መጨረሻ ስምምነት ለመድረስ በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ የሃሳብ ልውውጥ ተደርጓል።

በቀጣይም በጃንዋሪ 28 እና 29 በዋሽንግተን ዲሲ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን፣ በመካከል ባለው ጊዜ ወቅት የሶስቱም አገራት የህግ ባለሙያዎች የተወከሉበት ቡድን በህግ ማዕቀፎቹ ላይ የጋራ ምክክር እንደሚያካሂድ ተገልጿል። በሶስቱም አገራት መካካል የበለጠ መግባባት፣ መተባበር እና መተማመን እንዲዳብር በጋራ ለመስራት በመግባባት ስሜት ውይይቱ መጠናቀቁን በዋንሽግተን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም