በአማራ ክልል በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመት ከ300 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች ሥራ ተፈጠረ

65
ባህር ዳር ጥር 6 ቀን 2012 ኢዜአ በአማራ ክልል በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመት ከ300 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ሥራ መፈጠሩን የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ገለጸ። ቢሮው የግማሽ ዓመቱን የዕቅድ አፈፃፀም ከተጠሪ ተቋማት ጋር ለሁለት ቀናት በባህር ዳር ገምግሟል። የቢሮው ኃላፊ አቶ የሻምበል ከበደ በግምገማውላይ እንደገለጹት የክልሉ መንግሥት በግማሽ በጀት ዓመት ለወጣቶች ሥራ ለመፍጠር ከያዘው ዕቅድ 57 ከመቶውን አሳክቷል። ለወጣቶች ሥራው በዋነኝነት የተፈጠረው  በግብርና፣ በማምረቻ(ማኑፋክቸሪንግ)፣ በኮንስትራክሽን፣ በንግድ፣ በአገልግሎት ዘርፎች መሆኑን ተናግረዋል። በዕቅዱ 570ሺህ ወጣቶችን የሥራ ባለቤት ለማድረግ ታቅዶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ የሻምበል፣በዕቅዱ አፈጻጸም  የመስሪያና የመሸጫ ቦታ፣ የኤሌክትሪክ፣ የብድርና የቴክኖሎጂ አቅርቦት እጥረት እንዳጋጠሙ ገልጸዋል። የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ፀጋዎችን ለይቶ በቅንጅት ርብርብ  አለማድረግንም ሌላው ችግር እንደነበር አመልክተዋል። በተለይም የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት አነስተኛ መሆን፣ የኢንቨስትመንት አማራጭ ፕሮጀክቶች አለመኖር፣ ባለሃብቶች የጀመሯቸውን ፕሮጀክቶች አጠናቀው ወደ ሥራ አለመግባታቸው ችግሮች እንዳጋጠሙ ገልጸዋል። በዓመቱ ለአንድ ሚሊዮን ያሀል  ወጣቶች ሥራ ለመፍጠር መታቀዱን ኃላፊው አስታውቀዋል።በየደረጃው ዕቅዱን የሚያስፈጽም አመራርና ችግሮቹን ማረም ግን  ወሳኝ እንደሆነ በመጠቆም። የደቡብ ወሎ ዞን ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መኮንን በበኩላቸው በዞኑ ለ69 ሺህ ወጣቶች ሥራ ለመፍጠር ታቅዶ የተሳካው 36 በመቶ እንደሆነ አስታውቀዋል። በማምረቻ ኢንዱስትሪና በማዕድን ዘርፎች ደግሞ የተሻለ ሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸው፣ በእንስሳት ሃብትና በኮንስትራክሽን ዘርፎች የታቀደው ግን እንዳልተሳካ አመልክተዋል። በቀሪው ግማሽ ዓመት ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅተው በመንቀሳቀስ ውጤት ለማስመዝገብ  ጥረት ይደረጋል ብለዋል። በዕድገት ተኮር ዘርፎች ለወጣቶች ቋሚ ሥራ ለመፍጠር እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ በላቸው ንጉሴ ናቸው። በግማሽ ዓመቱ የዕቅዳቸውን 58 በመቶ ማሳካታቸውንም ገልጸዋል። ዞኑ የኢንዱስትሪ መዳረሻ እየሆነ በመምጣቱ ወጣቶቹ ከቋሚ ቅጥር በሻገር፣ በምግብና ምግብ ነክ፣ በኮንስትራክሽንና ሌሎች መስኮች መሰማራታቸውን ተናግረዋል። ቢሮው የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካትም የአንድ ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር የሥራ ፈጠራ በጀት አዘጋጅቶ ለክልሉ መንግሥት ማቅረቡን የቢሮው መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም