የማጃንግ ዞን አመራር ሰላም ለማረጋገጥና ልማትን ለማፋጠን እንዲሰራ ተጠየቀ

85

ጋምቤላ ጥር 6 ቀን 20129 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የማጃንግ ዞን አመራር ሰላም ለማረጋገጥና ልማትን ለማፋጠን እንዲሰራ የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አሳሰቡ።

በዞኑ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አመራሮችና ተቋማት ሕዝቡ የእውቅናና ምስጋና መርሐ ግብር አዘጋጅቷል።

አፈ- ጉባዔው አቶ ላክድር ላክባክ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት አመራሩ የዞኑ ህዝብ በሰላም ግንባታና የልማት ስራዎች እያሳየ ያለውን ተሳትፎ  ማጠናከር ያስፈልጋል።

አመራሩ ለዞኑ ዘላቂ ሰላምና ልማት ሕዝብን ባሳተፈ መንገድ እንዲሰራ አስገንዝበዋል።

ከአራት ዓመታት በፊት በዞኑ የነበረው ችግር ተወግዶ አሁን አስተማማኝ ሰላም የሰፈነው አመራሩና ህዝቡ ተባብሮ በመስራታቸው ነው ብለዋል።

በተለይም በህዝቡ ለአመራሩና ለተቋማቱ ያዘጋጀው የምስጋናና የእውቅና መርሐ ግብር ህዝቡ ለዞኑ ዘላቂ ሰላምና ልማት ያለውን አጋርነት እንደሚያሳይ አፈ ጉባዔው ገልጸዋል።

በመሆኑም አመራሩ በተለይም በህዝቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንዲሰራ አስገንዝበዋል።

በህዝቡ የተሰጠው እውቅናና ምስጋና ለአመራሩ ተጨማሪ አደራና ኃላፊነት ጭምር መሆኑን አቶ ላክድር ተናግረዋል።

የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ማህበር ኮር በበኩላቸው በዞኑ ያለውን አስተማኝ ሰላም በመጠበቅ የልማትና የለውጥ ጉዞውን ለማፋጠን አመራሩና ህዝቡ ተቀናጅተው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የዞኑን  የሰላምና የልማት ስራዎች ልምድ  ሌሎች ዞኖችና ወረዳዎች በተሞክሮነት እንዲወስዱት አሳስበዋል።

ከክልሉ ብሎም ከአገሪቱ የለውጥ ጉዞ ጋር አጣጥመው እንዲጠቀሙበት ተወካዩ አስገንዘበዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ ሙሴ ጋጃት በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በዞኑ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነው በአመራሩ ብቻ ሳይሆን፣ በህዝቡ ተሳትፎ ታግዞ እንደሆነ ገልጸዋል።

በቀጣይም የህዝቡን የሰላምና ልማት አጋርነት ለማጠናከር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

በህዝቡ የሰጣቸው የእውቅናና የምስጋና ሽልማት ለበለጠ ስራና የህዝብ አገልጋይነት እንደሚያነሳሳቸው የጠቆሙት አቶ ሙሴ፣ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ከእውቅናና የምስጋና መርሐ ግብሩ አዘጋጆች መካከል አቶ እንደሻው ውበት እንዳሉት መረሃ ግብሩ የተዘጋጀው በዞኑ ሰላም ለማስፈን የሰሩ አመራሮችንና ተቋማትን ለማበረታታት ነው።

በተጨማሪም በዞኑ የተፈጠረው አስተማማኝ ሰላም ለሌሎች ተጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ተሞክሮ እንዲሆን በማሰብ ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል።

በቀጣይም ህዝቡ ከአመራሮች ጎን በመሰለፍ ለሰላምና ለልማት ስራዎች ስኬት እንደሚሰሩ አቶ እንደሻው ገልጸዋል።

በዞኑ በ2007 ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር ያስከፈለውን ዋጋ በመገንዘብ ከአመራሩ ጋር በቅንጅት በመስራት የዞኑን ሰላም ወደ ነበረበት መመለሱን የገለጹት ደግሞ ሌላው የመርሐ ግብሩ አዘጋጅ ኮሚቴ  አባል አቶ ኛሞል ባልዲ ናቸው።

በሜጢ ከተማ በተዘጋጀው መርሐ ግብር ለዞንና ለወረዳ የአመራር አካላትና ተቋማት የምስክር ወረቀትና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተጎረባች ክልሎችና የክልሉ የዞን፣ የወረዳ ተወካዮች ታዳሚዎች ነበሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም