የእምነት ተቋማት በተጠና እና በተደራጀ መልኩ ተከታዮቻቸውን ማስተማር ይገባቸዋል

56
አዲስ አበባ ጥር 6 ቀን 2012 (ኢዜአ) የእምነት ተቋማት በተጠና እና በተደራጀ መልኩ ተከታዮቻቸውን በማስተማር ለአገር ሰላምና መረጋጋት መስራት እንደሚገባቸው ተገለፀ። የኢትዮጵያ መፅሃፍ ቅዱስ ማህበር የክርስትና እምነት አባቶችና የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የሚሳተፉበት በአገር ሰላምና በማህበረሰብ አንድነት ዙሪያ ለሁለት ቀናት ውይይት እያደረገ ነው። የኢትዮጵያ መፅሃፍ ቅዱስ ማህበር ጠቅላይ ፀኃፊ አቶ ይልማ ጌታሁን የእምነት ተቋማት በተጠናና በተደራጀ አኳኋን ለተከታዮቻቸው ትምህርት በመስጠት ለአገር ሰላምና መረጋጋት መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ወደ እምነት ቦታዎች የሚሄደውን ምዕመን በሰፊው ለማስተማር የሃይማኖት መሪዎች አቅደው በመስራት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን መትጋት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። ማህበሩ በአገር ሰላምና መረጋጋት ላይ ከክርስትና እምነት ተከታዮች ውጭ ከሆኑ የእምነት ተቋማት ጋር ለመስራት ሁኔታዎችን እያመቻቸ እንደሆነ አቶ ይልማ ገልፀዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ኃላፊ መሪጌታ መሐሪ  ሃይሉ ሁሉም የእምነት ተቋማት ለአገር ሰላምና መረጋጋት ሲባል በመቀራረብ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የአንደኛው እምነት ተከታይ ሲያጠፋ ለአገር አንድነትና ሰላም የሚያመጣውን ችግር በመረዳት በጋራ ሆኖ በመስራት መፍትሄ ማምጣት እንደሚገባ ተናግረዋል። ''በአሁኑ ወቅት አገራችን ያለችበትን የሰላም እጦት በመረዳት እስካሁን  ከነበረው በላይ የእምነት ተቋማት ተቀራርበን መስራት አለብን'' ብለዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ መምህር ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው የእምነት ተቋማት መሪዎች የቤተክርስትያንን ቀኖናና ስርዓት በማይቃረን መልኩ ዘመኑን መሰረት ያደርገ ትምህርት በማስተማር ለአገር ሰላምና መረጋጋት እንዲሰሩ ጠይቀዋል። በተመሳሳይ የአገር መሪዎችም ከተለመደው አሰራር ወጥተው ወጣቶችን ከችግር ለማውጣት የተጠናና የተደራጀ ስራ መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ መፅሃፍ ቅዱስ ማህበር በ1917 ዓ.ም ተመስርቶ መፅሃፍ ቅዱስ በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ የእምነቱ ተከታዮች ማግኘት የሚገባቸውን መንፈሳዊ ትምህርት እንዲያገኙ እየሰራ ይገኛል። በተጨማሪም በአገር ሰላምና በማህበረሰብ አንድነት ላይ እንደሚሰራ ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም