የተጓተቱ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቷል--የኦሮሚያ ክልል መንግስት

87
ጥር 6 ቀን 2012 በኦሮሚያ ክልል በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ ያልተጠናቀቁ የመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በአፋጣኝ ለማጠናቀቅ ትኩረት መስጠቱን የክልሉ መንግስት አስታወቀ። የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በቡኖ በደሌና ኢሉአባቦር ዞኖች በግንባታ ላይ ያሉ የገጠር መንገዶችን ዛሬ ተዘዋውረው ተመልክተዋል። በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የግብርና ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ግንባታቸው የተጓተቱትን  ግንባታዎችን ፈጥኖ ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቷል። "የክልሉ መንግስት ተጨማሪ ባጀት ከመመደብ ጀምሮ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን በማጠናከር ግንባታዎቹን ለማጠናቀቅ እየሰራ ነው "ብለዋል። በኢሉአባቦር ዞን በያዮ ወረዳ እየተገነባ ያለው የያዮ-ኤሌሞ 29 ኪሎ ሜትር መንገድን ጨምሮ በክልሉ ሰባት የገጠር መንገድ ግንባታዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዳልተጠናቀቁ ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ በኢሉአባቦር ዞን የያዮ-ኤሌሞና በቡኖ በደሌ ዞን የያንፋ -ጎንቦሮ የገጠር መንገድ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የክልሉ መንግስት የተጓተቱ የመንገድ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ ግማሽ ቢሊዮን ብር መመደቡን ዶክተር ግርማ ተናግረዋል። በያዩ ወረዳ ከ47 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት ግንባታው በ2007 ተጀምሮ ያልተጠናቀቀ የንፁህ ውሃ ተቋም እስከ በጀት አመቱ መጨረሻ ድረስ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። እንደ ዶክተር ግርማ ገለጻ ለመሠረተ ልማት ግንባታዎች መጓተት ምክንያት የሆኑ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል። የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ረጋሳ በበኩላቸው "በዞኑ ግንባታቸው የተጓተቱ የመሰረተ ልማት ስራዎች እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ እንዲጠናቀቁ ይደረጋል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም