በደቡብ ክልል የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ አብዛኛውን መቆጣጠር ተችሏል

57
ሀዋሳ ጥር ፣6/ 2012 (ኢዜአ)  በደቡብ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተ የአንበጣ መንጋ በአብዛኛው በቁጥጥር ስር መዋሉን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ምክትልና የእርሻ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው እንደተናገሩት ክልሉን ከሚያዋስነው ከኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ በኩል የገባ የአንበጣ መንጋ ባለፈው እሁድ በቡርጂ ልዩ ወረዳ በ10 ቀበሌዎች ተከስቷል፡፡ ኅብረተሰቡን በማስተባበር በተደረገ ባህላዊ የመከላከል ዘዴ ሁሉንም ቀበሌዎች ከአንበጣው ነጻ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በኩል የመጣ የአንበጣ መንጋም በክልሉ አማሮ ልዩ ወረዳ በአንድ ቀበሌ በመከሰቱ በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በባህላዊ መንገድ መቆጣጠር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል ። በሌሎች የክልሉ አቅጣጫዎችም የአንበጣ መንጋ ሊከሰት የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩን ያመለከቱት ኃላፊው፣ ሥጋት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ በባለሙያዎች ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ የአንበጣ መንጋው በሰብል ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም። ቢሮው መንጋውን ለመከላከል ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት አስፈላጊ በሚሆንበት ሰዓት በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ ዝግጅት ማድረጉን አቶ ዳንኤል ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም