በሃረሪ ክልል ሶስት ወረዳዎች የተከሰተው አንበጣ በቁጥጥር ስር ውሏል...የክልሉ ግብርና ቢሮ

57
ኤዜአ ጥር 6/2012 በሐረሪ ክልል የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ። የቢሮው የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሚር ሙሳ እንደተናገሩት በሶስት ወረዳዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ህዝቡን ባሳተፈ ባህላዊ የመከላከያ ዘዴ በቁጥጥር ስር ውሏል። በክልሉ የደረሰ ሰብል አስቀድሞ የተሰበሰበ በመሆኑ የአንበጣ መንጋው በሰብል ላይ ጉዳት እንዳላደረሰም ተናግረዋል። "በአሁኑ ወቅትም በስምንት ቀበሌ ገበሬ ማህበራት የአንበጣው መንጋ እንቁላል የጣለበትን ስፍራ ዳግም እንዳይፈለፈልና ተመልሶ እንዳይከሰት በባለሞያ የታገዘ የማጣራት ስራ እየተከናወነ ይገኛል"ብለዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል የሚሰራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሌሎች የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አቶ አሚር ተናግረዋል። በክልሉ የሶፊ ወረዳ የግብርና ባለሞያ አቶ ረመዳን አልይ እንደገለጹት የአንበጣው መንጋ በወረዳው ለሁለት ቀናት ያክል ተከስቷል። "አርሶ አደሩን ፣ ህብረተሰቡንና ተማሪዎችን በማደራጀት በጭስ ፣በጩኽትና በሌሎች በባህላዊ ዘዴዎች በመታገዝም በዘመቻ ማጥፋት ችለናል" ብለዋል። እንደሌሎቹ አካባቢዎች ሁሉ በዚህ ወረዳም የደረሱ ሰብሎች ቀደም ሲል በመሰብሰባቸው የአንበጣው መንጋ በሰብል ላይ ጉዳት አለማስከተሉን ገልጸው ተመልሶ እንዳይመጣም በባለሞያ የመከታተል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የአንበጣ መንጋው ከየመን እና ሶማሌላንድ በምስራቁ የሃገራችን ክፍል እየገባ በተለያዩ ክልሎች የግብርና ስራዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖውን ማሳረፉን ይታወቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም