የወላይታ ዲቻ ስፖርት ክለብ አመራሮች ከኃላፊነት ተነሱ

63
ሶዶ ኢዜአ ጥር 5 / 2012  የወላይታ ዲቻ ስፖርት ክለብ ቦርድ የክለቡን ከፍተኛ አመራሮች ከኃላፊነት አነሳ። ቦርዶ አመራሮቹን ከኃላፊነት ያነሳው ትላንት ማምሻውን ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ነው። ቦርዱ ከኃላፊነት ያነሳቸው ክለቡን ከ2004 ዓም ጀምሮ በስራ አስኪያጅነት ሲመሩ የነበሩ አቶ አሰፋ ሆሲሶ፣ የክለቡ የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አንዱዓለም ሽብሩና የክለቡ የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ታደሰ መታፈሪያ ናቸው። የወላይታ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የስፖርት ክለቡ ቦርድ ፕሬዝዳንት አቶ ጎበዜ ጎዳና የቦርዱን ወሳኔ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ  አመራሮቹን ከኃላፊነት ማንሳት ያስፈለገው ክለቡን እየገጠመው ካለው የውጤት ማሽቆልቆል ለመታደግ ነው። በክለቡ ለማለያ ፍቅርና ክብር መንሳት፣ የተነሳሽነት ስሜት ማጣት ፣ የቡድን ስሜት መውረድና መሰል ችግሮች መበራከታቸውን ተናግረዋል። የስፖርቱን ቤተሰቡን ስሜት ያለማዳመጥና የቦርዱን ውሳኔ ያለማክበር የስነ-ምግባር ጉድለትም መስተዋላቸውን ጠቅሰዋል ። "አመራሮቹ  ክለቡን ካጋጠው ችግር ማውጣት እንዳልቻሉ በግመገማ በመረጋገጡ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተወስኗል" ብለዋል ። ክለቡ በሜዳው ባካሄዳቸው ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች "ማሸነፍ ካልቻልኩ በገዛ ፈቃዴ እለቃለሁ" ብለው የነበሩት የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በስሁል ሽሬ ከገጠማቸው ሽንፈት በኋላ በስራ ገበታቸው ባለመገኘታቸው የጥሪ ማስታወቂያ እንደወጣባቸው ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ አሰልጣኙ በማስታወቂያው መሠረት በስራ ገበታቸው ካልተገኙ ጉዳዩ በፌደሬሽን ህግ መሠረት የሚዳኝ ይሆናል። በቦርዱ ውሳኔ መሠረት ከቦታቸው በተነሱ አመራሮች ምትክ ቋሚ አመራሮች እስኪተኩ ድረስ አቶ ምትኩ ሀይሌ በዋና ሥራ አስኪያጅነት፣ አቶ ሚካኤል ዋዳ የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንትና አቶ ዘላለም ማቴዎስ በቴክኒክ ዳይሬክተርነት ቦታ መወከላቸውን ተናግረዋል። ከዋና አሰልጣኙ ጋር ያለው ጉዳይ እስኪጠናቀቅ ድረስ በህጉ መሠረት ምክትል አሰልጣኝ የነበሩት ደለለኝ ደቻሳ ጃምቦ የዋና አሰልጣኝነት ውክልና ተሰጥቷቸው ቀጣይ ጨዋታዎችን እንዲመሩ መወሰኑን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም