የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ውጤት

120
ኢዜአ ጥር 5/2012 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትናንትና ዛሬ በክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ ተካሄደዋል። ጨዋታዎቹ የተደረጉት የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ከትናንት በስቲያ በነበረው ጠቅላላ ጉባኤ ምክንያት የቀን ሽግሽግ ተደርጎባቸው ነው። በዚሁ መሰረት ዛሬ በክልል ከተሞች ሶስት ጨዋታዎች ተካሄደዋል። መቐለ ላይ መቐለ ሰብዓ እንደርታ መከላከያን 36 ለ 21 ሲያሸንፍ፤ ጎንደር ላይ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጎንደር ከተማን 30 ለ 23  ረቷል። ቦንጋ ላይ ቡታጅራ ከተማ አዲሱ የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ሚዛን አማንን 28 ለ 18 አሸንፏል። ሁለቱ ክለቦች ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ሚዛን አማን ከተማ ላይ የነበረ ቢሆንም በከተማው በጣለው ዝናብ ጨዋታው በቦንጋ ከተማ እንዲካሄድ መደረጉን የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። በፕሪሚየር ሊጉ ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፌደራል ማረሚያ ቤቶችን 32 ለ 29 ሲረታ፤ ከምባታ ዱራሜ ፌደራል ፖሊስን 27 ለ 28  አሸንፏል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ፣መቐለ ሰብዓ እንደርታ፣ቂርቆስ ከፍለ ከተማና ከምባታ ዱራሜ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከአንድ አስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። አዲሱ የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ሚዛን አማን በ36 የግብ እዳ የመጨረሻውን 10ኛ ደረጃ ይዟል። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ጥር 9 እና 10 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም